Proof Bible is word of God p 2, read in pdf
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ የሚያስረዱትን ውስጣዊ ማረጋገጫና ከውጫዊ ማረጋገጫዎች የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስን ተከታታይነትና ወጥነት ባለፈው አይተን ቀሪውን በዚህ ክፍል እናያለን።
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ የሚያስረዱትን ውስጣዊ ማረጋገጫና ከውጫዊ ማረጋገጫዎች የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስን ተከታታይነትና ወጥነት ባለፈው አይተን ቀሪውን በዚህ ክፍል እናያለን።
ለ. የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ ጥልቅነት፡- እውነትን በመግለጥ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርምሮ አያልቅም። ቴሌስኮፕ የሰማይን ከፍታ እንደሚያሳይ፡ መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራዎች ከመነሻ እስከ ፍጻሜ፡ ከሰማይ ከፍታ እስከ ሲኦል ጥልቀት ያመለክታል። ማይክሮስኮፕ ረቂቅ ነገሮችን እንደሚያሳይ ሁሉ ረቂቁ የእግዚብሔር፥ ሥራ ዕቅድና ዓላማው እንዲሁም የፍጥረቱ ፍጹምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት ብዙ መጻሕፍት የተጻፉት ጸሐፊዎቹ ስለዘመናዊው ግኝት ግምት ባልነበራቸው ጊዜና በጥንታዊው የሰው ልጅ እውቀት ደረጃ ቢሆን፡ በቅርቡ የተገኙት የሥነ-ምድር ምርምር ጥናቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች ከመቃረን ይልቅ ይደግፋሉ። ጥንታዊዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚያስደንቅ አኳኋን ከዘመናዊው የሥነ-ምድር ምርምር ግኝቶች ጋር ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ዘላለማዊነት ያላቸውንና በእግዚአብሔር ብቻ የሚታወቁትን እውነቶች ስለሚገልጥ፥ ከሰው ምርምርና ግኝት በላይ የሆኑ እውነቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በሙላትና በረቂቅነት የሚያሳየንን ያህል የሚያሳይ ሌላ መጽሐፍ በዓለም የለም።
ሐ. የመጽሐፍ ቅዱስ የመለወጥ ኃይልና ኅትመቱ፡ በዓለማችን የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ለተለያዩ ሕዝቦችና ባሕሎች በተለያዩ አያሌ ቋንቋዎች የታተመ ሌላ መጽሐፍ የለም። የማተሚያ መኪና እንደተፈለሰፈም ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች ሁሉ በብዙ ሚሊየን ቅጂዎች ታትሟል። ጽሑፍ ያለው እያንዳንዱ ቋንቋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ ጥቂት ክፍሎች የታተመ ነገር አለው። ምንም እንኳን እንደ ፈረንሳዊው ቮልቴር ያሉ ሃይማኖት የለሾች መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በኋላ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል ቢሉም፥ የሀያኛው ክፍለ-ዘመን ደራሲያንም መጽሐፉ ይረሳል ወይም ፈላጊ አይኖረውም ቢሉም፥ ካለፈው ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች በመታተም ላይ ነው። በተከታዮች ብዛት ከክርስትና የሚበልጡ ሌሎች ሃይማኖቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊወዳደር የሚችልና መገለጥ ያለው ጽሑፍ ሊያቀርቡ አልቻሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን የመለወጥ ኃይል በዘመናችንም ቀጥሏል።