Wednesday, March 21, 2012

የጥያቄ ፬ መልስ (ክፍል ፩)


4. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድን ነው?
 Proof the Bible is Word of God part-1,READ IN PDF

መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ የብዙ ዓመታት ታሪክ የሚያጠቃልል ሲሆን ከአርባ በሚበልጡ በተለያዩ ዘመናትና ሁኔታዎች ውስጥ ባለፉ ሰዎች የተጻፈ ነው። ይሁን እንጂ የማይገናኙ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ስብስብ ሳይሆን አስደናቂ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚደግፉ ሁለት ማረጋገጫዎች አሉ።  ፩. አንዱ ውስጣዊ ማረጋገጫ ነው። ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመለከቱት እውነታዎችና መጽሐፉ ራሱ ስለመለኮታዊነቱ የሚገልጠው ሲሆን፣  ፪. ውጫዊ ማረጋገጫ ደግሞ ልዐለ-ተፈጥሮ የሆነውን ባሕርይውን የሚገልጹ ውስጡ የተጠቀሱት እውነቶች ናቸው።

፩. ውስጣዊ ማረጋገጫ፡-
 መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በመቶ በሚቆጠሩ የንባብ ክፍል ራሱ አረጋግጦአል። የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ክርስቶስም ጭምር መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ገላጭነት የተጻፈ ነው ይላሉ።
  «ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።» ዮሐ ፪፡፳፪
« ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።»  ፩ተሰ ፪፡፲፫።


« የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ነፍስን ይመልሳል የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።
የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል።» መዝ ፲፱፡ ፯-፰።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግ መፈጸም እንደነበረበት ራሱ ተናግሯል።
« እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። » ማቴ ፭፡፲፯።
እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በተለያየ መንገድ ለነቢያቱ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በልጁ ቃሉን የተናገረ መሆኑን የዕብራውያን ጸሐፊ ይናገራል።
« ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥
ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ » ዕብ ፩፡፩-፪።

፩. ውጫዊ ማረጋገጫ፡-
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በራሱ የሚያስረግጥ ብቻ ሳይሆን ተጠራጣሪዎችን እንኳን ለማሳመን በሚችሉ ብዙ መረጃዎች የተሞላ ነው፡፡

ሀ. የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታታይነት እና ወጥነት፡- ስለመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጡት እጅግ አስገራሚ እውነቶች አንዱ ወደ 1600 ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ በኖሩና ከአርባ በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ሰዎች የተጻፈ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፉ የስድሳ ስድስት መጻሕፍት ስብስብ ሳይሆን፡ አንድና ወጥ ነው። ጸሐፊዎቹ ከተለያየ ማኅበራዊ መሠረት የመጡ ናቸው፤ ነገሥታት፡ ጭሰኞች፡ ፈላስፋዎች፡ ዓሣ አጥማጆች፡ ሐኪሞች፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት፡ ምሁራን፡ ባለቅኔዎች እና ገበሬዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ባሕሎችና ልምዶች መኖር ብቻ ሳይሆን፡ የተለያዩ ባሕርያትም ነበሯቸው። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በግልጥ የሚታይ ተከታታይነትና ወጥነት አለው።

የመጽሐፉ ተከታታይነት ከአሁኑ ዓለም አፈጣጠር እስከ አዲሱ ሰማይና ምድር መፈጠር ድረስ ባለው ታሪካዊ ቅደም ተከተል ሥርዓት ሊታይ ይችላል። ብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ፡ ስለኃጢአት፡ ስለድኅነት፡ እነዲሁም እግዚአብሔር ስለ መላው ዓለም፥ ስለእስራኤልና ስለቤተ ክርስቲያን ያለውን ዓላማና ዕቅድ ይገልጣል። መለኮታዊ ትምህርት ከዝቅተኛው፥ ማለት ቀለል ካለ መግቢያ ተነሥቶ እስከተወሳሰበ ትምህርትነት ደረጃ በደረጃ ይቀርባል። መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ አገላለጦችን በቀጥተኛ ትርጉማቸው፥ ትንቢቶችን ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ክንውናቸው ያሳያል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ፥ በሰማይና በምድር እጅግ ስለከበረውና ፍጹም ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድሚያ መተንበይ፥ የትንቢቱን እውንነት ማመልከትና ኢየሱስን ከፍ ማድረግ ነው። ይህ አስደናቂ መጽሐፍ በሰዎች ተጻፈ ብሎ ከማመን ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ገላጭነት ተጻፈ የሚለውን መቀበሉ ይቀልላል። ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ሁሉ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች በተለያዩ ሰዎች የተጻፉ መሆናቸውን በመቀበል፡ የመልእክቶቹን አንድ ወጥነት በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና አነሳሽነት ይረዳሉ።
(ይቀጥላል)


No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment