Monday, October 31, 2011

ጥያቄ-፪

ይህ ክፍል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ጥያቄዎችን የምንወያይበት ነው።
ባለፈው በጥያቄ ፩ - እግዚአብሔር  አዳምን  ከመፍጠሩ  በፊት  አዳም  እንደሚሳሳት ያውቃል/  አያውቅም? እንደሚሳሳት  ካወቀ ለምን  ፈጠረው?  የሚለውን ማየታችን ይታወሳል:: ለዛሬ ወደ ጥያቄ ፪  እናልፋልን::
፪ -  ዕጸ-በለስ  ባትኖር አዳም አይሳሳትም ነበር?   እግዚአብሔር ለምን ዕጸ-በለስን ፈጠረ? ወይም ለምን እንዳይበላ ከለከለ?


ለዚህ ጥያቄ ተሳታፊዎች ከዚህ ጽሑፍ ሥር comments የሚለውን በመጫን post comment በሚለው መልሳችሁን መላክ ትችላላችሁ።  መልሱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይሰጣል።

Tuesday, October 25, 2011

የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱ ዋና ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን


መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ ይዘቱ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ተግባራት እንዲሁም ከሰዎች ምን እንደሚፈልግ የሚናገር መሆኑን እና ከዓለም መፈጠር እስከ ዓለም ማለፍ ያሉ ክስተቶችን እንደሚያካትት ባለፈው ጽሑፋችን አይተናል። ይህ ታላቅ መጽሐፍ ሁለት ታላላቅ ክፍሎችን የያዘ ነው። ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን።

የኪዳናቱ ስያሜ
ብሉይ- ማለት አሮጌ/ያረጀ/የቆየ።  አዲስ - ማለት አዲስ  ነው።
ኪዳን- ማለት ውል / ስምምነት ማለት ነው።
ስለዚህ ብሉይ ኪዳን- የቆየ ውል ስምምነት/ አዲስ ኪዳን - አዲስ ውል/ስምምነት ማለት ነው። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከወዳጆቹ ጋር ያለው ግንኙነት በቃል ኪዳን ላይ የተመሠረተ ነው። ከኖኅ፡ ከአብርሃም… ጋር ያደረጋቸውን ቃል ኪዳኖች ያስተውሏል።
ብሉይ ኪዳን ብሉይ ኪዳን የሚለውን ስያሜ ያገኘው እግዚአብሔር ከመረጣቸው ሕዝብ ከእስራኤላውያን ጋር በሙሴ በኩል ባደረገው ቃል-ኪዳን  ነው። ቃል ኪዳኑም የተመሠረተው በእንስሳት ደም ነው።
«… የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው። እነርሱም፡- እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፡ እንታዘዛለንም አሉ። ሙሴም ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፡- በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።» ዘጸ ፳፬፡ ፩-፰
ስለዚህ ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ያደረገው ስምምነት ነው።

Saturday, October 15, 2011

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ይዘት


Over view of the Bible, READ IN PDF here
ባለፈው ጽሁፋችን የመጽሐፍ ቅዱስን አመጣጥ አይተን ስለመጽሐፍ ቅዱሰ ዋጋ ጥያቄ መጠየቃችን ይታወሳል።
ጥያቄውን ሌሎች አዲስ የሚገቡ የዚህ ውይይት አባላት እንዲመለከቱት መልሱን ከዚህ ውይይት ገጽ ላይ አናሰፍርም። ነገር ግን መልሱን ኢሜል አድራሻችሁን ከዚህ መልስ ሥር ብትጽፉልን እንልካለን።
ወደዛሬው ርዕሳችን ስንመለስ የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ይዘት እንዳስሳለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት በሰዎች ቋንቋ የተጻፈ ለሁሉም ዘመን፡ ለሁሉም ሰው የሚሆን የሕይወት ማዕድ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ፡ የቅኔ፡ የግጥም፡ የትንቢት፡ የመልዕክት… ክፍሎች በውስጡ አሉት። አከፋፈሉን ወደፊት በዝርዝር እናያለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለታሪክ ይናገራል። ስለታሪክ ቢናገርም ግን ሙሉ በሙሉ የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ስለሳይንስ ይናገራል። ነገር ግን የሳይንስ መጽሐፍ አይደለም። ስለፍልስፍናም ይናገራል። የፍልስፍና መጽሐፍ ግን አይደለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ይዘት በሦስት ዋና ክፍሎች ሊታይ ይችላል።
፩. ስለእግዚአብሔር ማንነት ይናገራል፡ ።ፈጣሪ፡ መጋቢ፡ ጠባቂ፡ ፈራጅ፡ አፍቃሪ ወዘተ… መሆኑን ።
፪. ስለእግዚአሔር ተግባራት፡- ከዚህ በፊት ምን እንዳደረገ፡ ወደፊት ምን እንደሚያደርግ፡
፫. ስለእግዚአብሔር ፍላጎት፡-  በአምሳሉና በአርአያው ከፈጠረው ከሰው ምን እንደሚፈልግ ይናገራል።
መጽሐፍ ቅዱስ በይዘቱ፡ አወቃቀሩ ከታሪክና ከጊዜ ቅደም ተከተል ጋር፡
·         በዓለም አፈጣጠር ይጀምራል። 
·         የዓለምን መዳን ማዕከል ያደርጋል።
·         በዓለም ማለፍ ይደመድማል።
* የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ገጽ የመጀመሪያው ዓረፍተ- ነገር፡  .. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ይላል - ዘፍ ፩፡፩
*  የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ገጽ የመጨረሸው ዓረፍተ-ነገር፡…
 .አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና። ብሎ በጸሎት ይደመድማል።  ራእ ፳፪፡ ፳
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም አፈጣጠር ይጀምርና በዓለም ፍጻሜ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይጨርሳል። ስለዚህ ከዓለም መፈጠር አንስቶ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የተከናወኑትንና የሚከናወኑትን ጉዳዮች አካትቶ ይዟል ማለት ነው።
ይህ ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ ስለመላው ዓለም ና የሰው ዘሮች ታሪክ በሙሉ ይናገራል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ስለጥንታዊው የቻይና ሥልጣኔ አይናገርም።
በብሉይ ኪዳን በዓለም አፈጣጠር ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ ስለመላው ዓለም ይናገራል። ከኖኅ በኋላ በአብርሃም ይቀጥልና የአንድን ሕዝብ (የእስራኤልን) ታሪክ ይዞ ይሄዳል። ይህም በቤተሰብ ደረጃ በአብርሃም፡ ይስሐቅና ያዕቆብ ጀምሮ በሃገር ደረጃ እስራኤል ተብለው ከግብጽ  መውጣት፡ መማረክ፡ በዓለም መበተን… እያለ ይቀጥላል።   በሐዲስ ኪዳንም በክርስቶስ ልደት ይጀምርና በሐዋርያት በኩል ወንጌል እንዴት ወደዓለም እንደደረሰ በመናገር ስለመጨረሻው ዘመን ትንቢት በሚናገረው በዮሐንስ ራእይ ይጨርሳል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ታላላቅ ክፍሎችን ይዞአል። ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን። የእነዚህን መጻሕፍት ዋና ዋና የታሪክ ና የትምህርት ፍሰቶች ቅደም ተከተል በጥቅሉ እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሁፋችን የብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን አጠቃለይ ይዘት እናያለን።
---------------ይቆየን----------------

Friday, October 7, 2011

የመጽሐፍ ቅዱስ አመጣጥ፡


How the Bible comes along, READ IN PDF here መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ዘመን በተለያዩ ጸሐፍያን በብዙ ድካም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንደተጻፈ አይተናል። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ የተጠበቀም ጭምር  ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ጥቃቶች ተጠብቆ፡ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት፡ በራሱ በእግዚአብሔር እንክብካቤ ዘመናትን ተሻግሮ ከኛ የደረሰ ግሩም ድንቅ መጽሐፍ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጊዜ ተጽፎ ተጠርዞ ከሰማይ የወረደ መጽሐፍ አይደለም። በተለያየ ጥራዝ በተለያየ ቦታ የነበረና በኋላ በ፫ቱ ምዕት ፫፻፳፭ ዓ/ም በአንድ ላይ የተጠረዘ መጽሐፍ ነው። ጸሐፍያኑ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት
፩. ከነርሱ በፊት ስለተከናወኑት ነገሮች -- ሙሴ ኦሪትን እንደጻፈ
፪. እነርሱ ባሉበት ጊዜ ስለተከናወኑ ነገሮች--ጳውሎስ መልዕክታትን እንደጻፈ
፫. እነርሱ ካለፉ በኋላ ስለሚከሰቱ ነገሮች---ነቢያት ትንቢትን እንደጻፉ አድርገው ጽፈዋል፡፡
ብሉይ ኪዳን ተጽፎ የተጠናቀቀው በ1ሺ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው።
የመጀመሪያዎቹ ፭ቱ ኦሪት-- በ1400 ዓ/ዓ ፡
የመጨረሻው ትንቢተ ሚልክያስ-- በ400 ዓ/ዓ ተጽፈዋል።
ሐዲስ ኪዳን እስከ 100 ዓ/ም ድረስ ተጽፎአል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሲጽፉ ርእስ አልነበራቸውም። ለየመጽሐፍቱ ርእስ የተሰጠው፡-
-      በመጽሐፉ የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ወይም
-      መጽሐፉ በሚናገርለት ዋና ሰው ወይም
-      መጽሐፉን ጽፎታል ብለው ይገምቱት በነበረው ሰው ስም በመሰየም ነበር።
አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እንደሚናገሩት በመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት ውስጥ ምዕራፍና ቁጥሮች አልነበሩም።
ለመጽሐፍ ቅዱስ የምዕራፍ ክፍፍል የተሰጠው በ1228 ዓ/ም፡ ሲሆን የቁጥር ክፍፍሎች የተደረጉት ደግሞ በ1547 ዓ/ም ነበር።
የቤት ሥራ፡-
የመጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ አሁን ስንት ነው?
 ከመጽሐፍ ቅዱስ የአንዱን መጽሐፍ ለምሳሌ፡ የኦሪት ዘፍጥረትን መጽሐፍ ገጾች የሚተካከል ሌላ ተራ መጽሐፍ ዋጋ ስንት  ነው?
በዚህ መሠረት የመላው መጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ ስንት መሆን ነበረበት?
ታዲያ እንዴት እኛ አሁን በዚህ ዋጋ አገኘነው?
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሁፋችን የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ይዘት እናያለን።
---------------ይቆየን----------------