Saturday, October 15, 2011

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ይዘት


Over view of the Bible, READ IN PDF here
ባለፈው ጽሁፋችን የመጽሐፍ ቅዱስን አመጣጥ አይተን ስለመጽሐፍ ቅዱሰ ዋጋ ጥያቄ መጠየቃችን ይታወሳል።
ጥያቄውን ሌሎች አዲስ የሚገቡ የዚህ ውይይት አባላት እንዲመለከቱት መልሱን ከዚህ ውይይት ገጽ ላይ አናሰፍርም። ነገር ግን መልሱን ኢሜል አድራሻችሁን ከዚህ መልስ ሥር ብትጽፉልን እንልካለን።
ወደዛሬው ርዕሳችን ስንመለስ የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ይዘት እንዳስሳለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት በሰዎች ቋንቋ የተጻፈ ለሁሉም ዘመን፡ ለሁሉም ሰው የሚሆን የሕይወት ማዕድ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ፡ የቅኔ፡ የግጥም፡ የትንቢት፡ የመልዕክት… ክፍሎች በውስጡ አሉት። አከፋፈሉን ወደፊት በዝርዝር እናያለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለታሪክ ይናገራል። ስለታሪክ ቢናገርም ግን ሙሉ በሙሉ የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ስለሳይንስ ይናገራል። ነገር ግን የሳይንስ መጽሐፍ አይደለም። ስለፍልስፍናም ይናገራል። የፍልስፍና መጽሐፍ ግን አይደለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ይዘት በሦስት ዋና ክፍሎች ሊታይ ይችላል።
፩. ስለእግዚአብሔር ማንነት ይናገራል፡ ።ፈጣሪ፡ መጋቢ፡ ጠባቂ፡ ፈራጅ፡ አፍቃሪ ወዘተ… መሆኑን ።
፪. ስለእግዚአሔር ተግባራት፡- ከዚህ በፊት ምን እንዳደረገ፡ ወደፊት ምን እንደሚያደርግ፡
፫. ስለእግዚአብሔር ፍላጎት፡-  በአምሳሉና በአርአያው ከፈጠረው ከሰው ምን እንደሚፈልግ ይናገራል።
መጽሐፍ ቅዱስ በይዘቱ፡ አወቃቀሩ ከታሪክና ከጊዜ ቅደም ተከተል ጋር፡
·         በዓለም አፈጣጠር ይጀምራል። 
·         የዓለምን መዳን ማዕከል ያደርጋል።
·         በዓለም ማለፍ ይደመድማል።
* የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ገጽ የመጀመሪያው ዓረፍተ- ነገር፡  .. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ይላል - ዘፍ ፩፡፩
*  የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ገጽ የመጨረሸው ዓረፍተ-ነገር፡…
 .አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና። ብሎ በጸሎት ይደመድማል።  ራእ ፳፪፡ ፳
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም አፈጣጠር ይጀምርና በዓለም ፍጻሜ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይጨርሳል። ስለዚህ ከዓለም መፈጠር አንስቶ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የተከናወኑትንና የሚከናወኑትን ጉዳዮች አካትቶ ይዟል ማለት ነው።
ይህ ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ ስለመላው ዓለም ና የሰው ዘሮች ታሪክ በሙሉ ይናገራል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ስለጥንታዊው የቻይና ሥልጣኔ አይናገርም።
በብሉይ ኪዳን በዓለም አፈጣጠር ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ ስለመላው ዓለም ይናገራል። ከኖኅ በኋላ በአብርሃም ይቀጥልና የአንድን ሕዝብ (የእስራኤልን) ታሪክ ይዞ ይሄዳል። ይህም በቤተሰብ ደረጃ በአብርሃም፡ ይስሐቅና ያዕቆብ ጀምሮ በሃገር ደረጃ እስራኤል ተብለው ከግብጽ  መውጣት፡ መማረክ፡ በዓለም መበተን… እያለ ይቀጥላል።   በሐዲስ ኪዳንም በክርስቶስ ልደት ይጀምርና በሐዋርያት በኩል ወንጌል እንዴት ወደዓለም እንደደረሰ በመናገር ስለመጨረሻው ዘመን ትንቢት በሚናገረው በዮሐንስ ራእይ ይጨርሳል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ታላላቅ ክፍሎችን ይዞአል። ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን። የእነዚህን መጻሕፍት ዋና ዋና የታሪክ ና የትምህርት ፍሰቶች ቅደም ተከተል በጥቅሉ እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣዩ ጽሁፋችን የብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን አጠቃለይ ይዘት እናያለን።
---------------ይቆየን----------------

1 comment:

  1. Wow! kezi ene yemredaw techemari neger, bible yetetsafew bemdr behywet salen yegziabhern aserar endnreda new

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment