Tuesday, January 31, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፩

"....በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።" ሕዝ ፴፯፣፮ 
በሕይወት የመኖራችን ዓላማ እግዚአብሔርን ማወቅ ከሆነ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን ወይ?


ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና።  ሆሴዕ ፮፣ ፮
፩. እግዚአብሔርን ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው?
-      ለሕይወት ስኬት - ለምድራዊ አስቤዛ ኑሮ መሟላት?
-      ከኑሮ ጭንቀት ለመላቀቅ - ሰላምና እረፍት ለማግኘት?
-      ለጠቅላላ ዕውቀት/ለመረጃ?  - አለ ወይስ የለም? እውነቱን ለማወቅ- 


እግዚአብሔር ሲባል - ወደ አእምሮአችን / ወደ ምናባችን የሚመጣው ምስል ምንድን ነው?
o   በሩቅ በሰማይ ያለ- ቁልቁል የሚያይ ሽማግሌ መሰል…...?
o   በሥላሴ ስዕል እንዳሉት ፫ ተመሳሳይ የተቀመጡ ሽማግሌ መሰል.....?
o   ወይም ሌላ ምስል.......?

       እግዚአብሔርን ስናስብ ትዝ የሚለን ምንድን ነው?
- እግዚአብሔርን ወይስ ከእግዚአብሔር የሆኑ ነገሮችን፤ 
- እግዚአብሔር በሕይወታችን በኃይሉ እየሠራ ነው? ወይስ
በአእምሮአችን እንዲሁ የተቀመጠ ከብዙ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው?
- እግዚአብሔርን ነው ወይስ ስለእግዚአብሔር ነው የምናውቀው?
ስለጃንሆይ ልናውቅ እንችላለን፤ ጃንሆይን ግን ላናውቃቸው እንችላለን፤ አላየናቸውም፣ አላገኘናቸውምና።
- እግዚአብሔርን እናውቀዋለን? - እርሱስ ያውቀናል? - እንተዋወቃለን?
- እናናግረዋለን?  - ከሆነስ -- ይሰማናል? -- ይመልስልናል? - እንደሚመልስልን ይሰማናል?
ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ መልሳችን «አይ» ከሆነ - እግዚአብሔርን አላወቅነውም። ወይም ስለእግዚአብሔር ያወቅነው አልገባንም።

- እግዚአብሔር ሊታወቅ ይችላል? ወይስ አይችልም? –
የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።  የሐዋ ፲፯፣ ፳፫
እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።      ዮሐ ፬፣፳፪

እግዚአብሔርን የምናመልከው አውቀነው ነው? ወይስ ባይገባንም ማምለክ ስላለብን? ወይስ እንዲሁ በዘልማድ ሌሎች ስላደረጉት?

እግዚአብሔርን ማወቅ/አለማወቅ ያለው ተጽእኖ
-       በሕይወታችን ለነገሮች ቅድሚያ የምንሰጠው ካለን የእግዚአብሔርን እውቀት አንጻር ነው።
በደንብ ካወቅነው/ከገባን እንኖርለታለን። እንኖርበታለን። -- ካልሆነ እንደ ትርፍ/ተጨማሪ እናየዋለን።
- በሕይወታችን በሚገጥሙን ፈተናና እና ችግሮች የምንወስዳቸው ውሳኔዎች እግዚአብሔርን ምን ያህል እንደምናውቀው ያሳያሉ።
- ሕይወትን ለመኖር የሚያስመኘው ስኬቶቻችን ናቸው  - ወይስ በዓላማ መኖራችን?
የዚህ ዓለም ስኬት መጨረሻው ምንድን ነው?.. ምን ስናገኝ ነው በቃ የምንለው?
- በየዕለቱ/ በየጊዜው አእምሮአችን የሚይዘው ምንድን ነው? በልባችን እና በአእምሮአችን ሰፊውን ስፍራ የያዘው እግዚአብሔርን ከማወቅ / ካለማወቅ ጋር የሚያያዝ ነው።

አንድ ባለሃብት ለአንድ አገልጋይ ያለውን ሰፊ የልማት/ የእርሻ ቦታ ሲያስጎበኘው ከስፋቱ የተነሳ በአንድ ቀን ተጎብኝቶ ሊያልቅ አልቻለም። ኋላ ባለሃብቱ «እንዴት ነው? ምን ተሰማህ?» ብሎ የሙገሳ ቃል ሲጠብቅ አገልጋዩ፡ «ይህንን ሁሉ ሃብት ለማስተዳደር ልብህ በዚህ ስለሚጠመድ ያሳዝነኛል» አለው።
    የዚህ ባለሃብት ልብ አሁን እየኖረበት ካለ ዓለም ጋር የተቆራኘ ነው።
ለአሁኑ እና ለዘላለሙ፣ ላለውና ለሚመጣው ነገር ሁሉ የምንሰጠው ዋጋ/ቦታ ባለን የእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ነው።
...............ይቀጥላል..............


Tuesday, January 17, 2017

የጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም


ጥር ፱፣ ፳፻፱ ዓ/ም
መጠመቅ:~  በቤክ ትምህርት ቀጥተኛ ትርጉሙ -ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ነው።

ትርጉሙ ከጌታ ሞትና ትንሣኤ ጋር በመተባበር ረገድ የሚገናኝ ነው። ወደታች እንደምናየው።

 የጥምቀት ምሳሌነት በብሉይ ኪዳን

1, በኖህ ዘመን

 ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ው፤  የጴጥሮስ መልእክት ፫ : ፳~ ፳፩  (ጥምቀት ከትንሣኤ ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ወደታች እናየዋለን።)

-       ኖህ እና ቤተሰቡ በመርከብ ውስጥ በውሃ መካከል በማለፍ ከእግዚአብሔር ቁጣ እና ከጥፋት ዳኑ

 2, በእስራኤላውያን

ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 : 1~2

-      እስራኤላውያን በባሕሩ መካከል በማለፍ ከጠላት ጥፋት ዳኑ:

2ቱም የጥምቀት ምሳሌዎች የሚያሳዩን~ ከጥፋት ለማምለጥ በውሃ ውስጥ/ መካከል ማለፍን ነው።

የጥምቀት አማናዊነት በአዲስ ኪዳን

 1, የዮሐንስ ጥምቀት: ማቴ

 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ የማቴዎስ ወንጌል ፫ : ፲፩

ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ። የሉቃስ ወንጌል ፫ : ፫-፮

ዓላማ:~ ሰዎችን ለጌታ ለማዘጋጀት: በትንቢት እንደተነገረው

በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ። የሉቃስ ወንጌል ፫ : ፫-፮  (መቼም ይህ የሚያሳየው አውራ ጎዳናውን ሳይሆን የሰዎችን ሕይወት ነው።?

 ~ አዘቅት: ከፅድቅ የጎደለው / ፍሬ የሌለው ሕይወት

~ ተራራ /ኮረብታ: በራስ ፅድቅ የተሞላው /ትእቢት እና ትምክህት ያለበት

~ ጠማማ: አካሄዱን የሳተ

 ~ ሸካራ: ለሌላው የማይመች

 2, የጌታ ጥምቀት