Tuesday, January 17, 2017

የጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም


ጥር ፱፣ ፳፻፱ ዓ/ም
መጠመቅ:~  በቤክ ትምህርት ቀጥተኛ ትርጉሙ -ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ነው።

ትርጉሙ ከጌታ ሞትና ትንሣኤ ጋር በመተባበር ረገድ የሚገናኝ ነው። ወደታች እንደምናየው።

 የጥምቀት ምሳሌነት በብሉይ ኪዳን

1, በኖህ ዘመን

 ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ው፤  የጴጥሮስ መልእክት ፫ : ፳~ ፳፩  (ጥምቀት ከትንሣኤ ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ወደታች እናየዋለን።)

-       ኖህ እና ቤተሰቡ በመርከብ ውስጥ በውሃ መካከል በማለፍ ከእግዚአብሔር ቁጣ እና ከጥፋት ዳኑ

 2, በእስራኤላውያን

ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 : 1~2

-      እስራኤላውያን በባሕሩ መካከል በማለፍ ከጠላት ጥፋት ዳኑ:

2ቱም የጥምቀት ምሳሌዎች የሚያሳዩን~ ከጥፋት ለማምለጥ በውሃ ውስጥ/ መካከል ማለፍን ነው።

የጥምቀት አማናዊነት በአዲስ ኪዳን

 1, የዮሐንስ ጥምቀት: ማቴ

 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ የማቴዎስ ወንጌል ፫ : ፲፩

ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ። የሉቃስ ወንጌል ፫ : ፫-፮

ዓላማ:~ ሰዎችን ለጌታ ለማዘጋጀት: በትንቢት እንደተነገረው

በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ። የሉቃስ ወንጌል ፫ : ፫-፮  (መቼም ይህ የሚያሳየው አውራ ጎዳናውን ሳይሆን የሰዎችን ሕይወት ነው።?

 ~ አዘቅት: ከፅድቅ የጎደለው / ፍሬ የሌለው ሕይወት

~ ተራራ /ኮረብታ: በራስ ፅድቅ የተሞላው /ትእቢት እና ትምክህት ያለበት

~ ጠማማ: አካሄዱን የሳተ

 ~ ሸካራ: ለሌላው የማይመች

 2, የጌታ ጥምቀት


 ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። የማቴዎስ ወንጌል ፫ : ፲፫~ ፲፯

ዓላማ: ለአርአያነት እንጂ ለልጅነት አይደለም:

 3, የእኛ ጥምቀት

እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ የማቴዎስ ወንጌል ፳፰ : ፲፱-፳

ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። የማርቆስ ወንጌል ፲፮ : ፲፮

 የኛ ጥምቀት ዋነኛ ዓላማ ~ ከጌታ ሞትና ትንሳኤ ጋር ለመተባበር ነው:

ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ወደ ሮሜ ሰዎች 6 : 3~4

-       ጥምቀት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ነውእንዴት? በሁለት መንገድ ነው።

በትርጉሙ እንዳየነው እና በሥርዓቱ እንደሚፈጸመው፡-  ውሃ ውስጥ ስንገባ- ከሞቱ ጋር፣ ከውሃ ስንወጣ- ከትንሣኤው ጋር አንድ እንሆናለን ማለት ነው - እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ቃል።

 ~ ክርስቶስ በዚች ዓለም ለኃጢአት ሞተ፡-

o    እኛም በኃጢአት ከመሞታችን በፊት ለኃጢአት መሞት አለብን:

እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ። ሮሜ ፮፣ ፲፩

ሞት ማለት የማይመለስ /የማይቀለበስ መለየት ነው::  ስለዚህ ዳግም ላንመለስበት ሆነን ከተደጋጋሚ የኃጢአት ልምምድ መውጣት ማለት ነው::

 ~ ክርስቶስ በትንሳኤ ሕይወት ከመቃብር ተነሳ

o   እኛም በክርስቶስ በማመን ያገኘነውን አዲስ ሕይወት በዚህ ምድር የፅድቅ ፍሬ ለማፍራት በመለማመድ እንድንኖር ነው:

ዮሐንስ ሲያጠምቅ እንዳዘዛቸው: ለንስሃ የሚገባ ፍሬ ይጠበቅብናል

እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ የማቴዎስ ወንጌል ፫ : ፰

ይህም ፍሬ በጥረታችን የምናመጣው ሳይሆን በክርስቶስ በማመናችን ባገኘነው ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚመጣ ፍሬ ነው:። የመንፈስ ፍሬ ተብሎ በገላትያ ፭: ፳፪  በተጠቀሰው መሠረት በሕይወታችን ይገለፃል:: በቤተክርስቲያን በ፵ እና በ፹ ቀናችን ስንጠመቅ በሜሮን ቅባት ምሳሌ የታተምንበት መንፈስ ቅዱስ በኛ ውስጥ ታዲያ ሥራው ምንድን ነው? ይህን ፍሬ እንድናፈራ ማስቻል አይደለምን?

ይህ ፍሬ በመጨረሻ ክርስቶስ ሲመጣ የሚጠይቀን (፮ቱ ቃላተ ወንጌል) እና  ከዚያም በአቅማችን ልክ 30 / 60 / 100 ፍሬ ባፈራነው መሠረት ሽልማት የምናገኝበት ነው::

 እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። የዮሐንስ ራእይ ፳፪ : ፲፪

ፍሬ ከሌለን ግን ይህ የሚያሳየው ሕይወት እንዳልነበረን ይህም ማለት በክርስቶስ በትክክል እንዳላመንን ስለሆነ ፍርድ ያስከትላል::

በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። የዮሐንስ ወንጌል ፫ :፲፰

አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። የማቴዎስ ወንጌል ፫ : ፲

ጥምቀት ከሥነ ሥርዓትና እና ከግርግር ባለፈ እግዚአብሔርን የምናስከብርበት: በኑሯችን ፍሬ የምንገለጥበት:  ሌሎችንም እንድንጠቅም የሚያስችለን የሕይወት ለውጥ የሚያመጣ ወሳኝ የክርስትና መሠረት ነው::

ዲ/ን አብርሃም ዘመድኃኔዓለም / DAT 27

ጥር ፲ / ፳፻፰ ዓ/ም - ጎንደር

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment