Tuesday, March 27, 2012

የጥያቄ ፬ መልስ (ቀጣይ)


Proof Bible is word of God p 2, read in pdf
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ የሚያስረዱትን ውስጣዊ ማረጋገጫና ከውጫዊ ማረጋገጫዎች የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስን ተከታታይነትና ወጥነት ባለፈው አይተን ቀሪውን በዚህ ክፍል እናያለን።


ለ. የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ ጥልቅነት፡- እውነትን በመግለጥ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርምሮ አያልቅም። ቴሌስኮፕ የሰማይን ከፍታ እንደሚያሳይ፡ መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራዎች ከመነሻ እስከ ፍጻሜ፡ ከሰማይ ከፍታ እስከ ሲኦል ጥልቀት ያመለክታል። ማይክሮስኮፕ ረቂቅ ነገሮችን እንደሚያሳይ ሁሉ ረቂቁ የእግዚብሔር፥ ሥራ ዕቅድና ዓላማው እንዲሁም የፍጥረቱ ፍጹምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት ብዙ መጻሕፍት የተጻፉት ጸሐፊዎቹ ስለዘመናዊው ግኝት ግምት ባልነበራቸው ጊዜና በጥንታዊው የሰው ልጅ እውቀት ደረጃ ቢሆን፡ በቅርቡ የተገኙት የሥነ-ምድር ምርምር ጥናቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች ከመቃረን ይልቅ ይደግፋሉ። ጥንታዊዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚያስደንቅ አኳኋን ከዘመናዊው የሥነ-ምድር ምርምር ግኝቶች ጋር ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ዘላለማዊነት ያላቸውንና በእግዚአብሔር ብቻ የሚታወቁትን እውነቶች ስለሚገልጥ፥ ከሰው ምርምርና ግኝት በላይ የሆኑ እውነቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በሙላትና በረቂቅነት የሚያሳየንን ያህል የሚያሳይ ሌላ መጽሐፍ በዓለም የለም።

ሐ. የመጽሐፍ ቅዱስ የመለወጥ ኃይልና ኅትመቱ፡ በዓለማችን የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ለተለያዩ ሕዝቦችና ባሕሎች በተለያዩ አያሌ ቋንቋዎች የታተመ ሌላ መጽሐፍ የለም። የማተሚያ መኪና እንደተፈለሰፈም ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች ሁሉ በብዙ ሚሊየን ቅጂዎች ታትሟል። ጽሑፍ ያለው እያንዳንዱ ቋንቋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ ጥቂት ክፍሎች የታተመ ነገር አለው። ምንም እንኳን እንደ ፈረንሳዊው ቮልቴር ያሉ ሃይማኖት የለሾች መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በኋላ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል ቢሉም፥ የሀያኛው ክፍለ-ዘመን ደራሲያንም መጽሐፉ ይረሳል ወይም ፈላጊ አይኖረውም ቢሉም፥ ካለፈው ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች በመታተም ላይ ነው። በተከታዮች ብዛት ከክርስትና የሚበልጡ ሌሎች ሃይማኖቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊወዳደር የሚችልና መገለጥ ያለው ጽሑፍ ሊያቀርቡ አልቻሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን የመለወጥ ኃይል በዘመናችንም ቀጥሏል።


-  ላልዳነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ « የመንፈስ ሰይፍ ነው» ኤፌ ፮፡፲፯፡
- ለዳነው የሚያነጻ፡ የቅድስናና ድል አድራጊነት ኃይል ነው። ዮሐ ፲፯፡፲፯፡ ፪ቆሮ ፫፡፲፯-፲፰፤ ኤፌ ፭፡፳፭-፳፮
መጽሐፍ ቅዱስ የሕግና የሥነ-ምግባር ብቸኛው መለኮታዊ መሠረት እንደሆነ ይኖራል።

       መ. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣-  የመጽሐፍ ቅዱስ ከሰው ዕውቀት በላይ የሆነ ባሕርይ የሚታየው፣ ሊታወቅ የማይቻልን እውነት ግልጥና እንዲታወቅ አድርጎ ማቅረቡ ነው። ዘላለምን ማለት ሰው ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ተፈጥሮ ሳይቀር ይገልጣል። የእግዚአብሔር ባሕርይና ሥራዎቹም ተገልጠውበታል። እግዚአብሔር ለዓለም፥ ለእስራኤልና ለቤተ ክርስቲያን ያለው አሳብና ዘላለማዊ ዕቅዱ፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ውስጥ ተጠቃሏል። በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ገለጣ የመጨረሻ፡ ትክክልና ጊዜ የማይገድበው ነው። ሁለንተናዊ ባሕርይው አንባቢዎቹን ከጊዜና ከዘላለም ጋር በተዛመደ ነገር ብልሆች አድርጓቸዋል።

    ሠ. መጽሐፍ ቅዱስ በሥነ-ጽሑፍነቱ፡ በሥነ ጽሑፍነቱ ሲታይ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ምጡቅ ነው። ታሪካዊ ዘገባዎችን ብቻ ሳይሆን፥ ዝርዝር ትንቢቶችን፥ ውብ የሆኑ ቅኔዎችን፥ ልዩ ውበት ያለው ተውኔትን፥ የፍቅርና የጦርነት ታሪኮችን፥ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ላይ የሚነሱ ፍልስፍናዎችን ያጠቃልላል። የጸሐፊዎቹ መለያየት ከያዛቸው ጉዳዮች ስብጥር ብዛት ጋር ይስማማል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናት የኖሩትንና በሁሉም የእውቀት ደረጃ ላይ የነበሩትን ሰዎች የማረከ ጽሑፍ የለም።

ረ. የማያዳላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ለሰዎች እንዲያደላ አላደረገውም። ያለማመንታት የማንንም ኀጢአት እና ደካማነት ይገልጣል። ይህ ብቻ አይደለም፥ በራሳቸው በጎ ምግባር የሚታመኑ ፍጻሜያቸው ጥፋት መሆኑንም ያስገነዝባል። በሰዎች ብዕር ቢጻፍም፡ ከሰው ወደ ሰው ሳይሆን፡ ከእግዚአብሔር ወደ ሰው የተላለፈ መልእክት ነው። ስለ ምድራዊ ነገሮችና ስለ ሰዎች ልምምድ ቢገልጥም፥ የሰማይና የምድርን፥ የሚታዩና የማይታዩ ነገሮችን ፥ ስለ እግዚአብሔር የሚገልጡ እውነቶችን፡ ስለ መላእክት፡ ስለ ሰው፡ ስለጊዜና ዘላለም፡ ስለሞትና ሕይወት፡ ስለ ኃጢአትና ድኅነት፡ ስለ መንግሥተ ሰማያትና ሲኦልም በግልጥነትና በሥልጣን ያብራራል። እንዲህ ያለን መጽሐፍ ሰው መጻፍ ቢፈልግ እንኳን ያለመለኮታዊ ምሪት ሊጽፈው አይችልም ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ቢጻፍም እግዚአብሔር ብቻ ከሚሰጠው እርግጠኛነት ዋስትና እና ሠላም ጋር ከርሱ የተላከ ነው።

ሰ. የመጽሐፍ ቅዱስ ሉዓላዊ ባሕርይ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም ይልቅ እግዚአብሔር በልጁ በኩል እራሱን መግለጡን ያመለከተ፡ አካልነቱንና ክብሩን ያስገነዘበ ታላቅ መጽሐፍ ነው። እንደ ኢየሱስ ያለው ስብእና የሟች ሰው ፈጠራ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ፍጹምነቱ ከሁሉ የላቀ እንዲሁም ቅድስናና ጥበብ ያለው በመሆኑ የዚህ ምድር ሰው የሚገነዘበው አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ባሕርይ የኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ ታሪክ በመግለጥ ተረጋግጧል።

                   ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች  ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ ገጽ 15-18
                      በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር፡ ተርጓሚ ተክሉ መንገሻ
                      1995-2003 1ኛ እትም

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment