Tuesday, April 24, 2012

ትንሣኤና ሕይወት

Resurrection and Life, read in pdf here
«ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤» ዮሐ ፲፩፣፳፭
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዋናው ዓላማ ለሕይወት እንደሆነ ራሱ ባለቤቱ ይነግረናል። ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል አደረገ ስንል የሞት ተቃራኒ የሆነውን ሕይወትን ሰጠን ማለታችን ነው። ከትንሣኤ ቀጥሎ ያለው ሕይወት እርሱም ሞት የማይከተለው የዘላለም ሕይወት ነው። ትንሣኤ እና ሕይወት።
ሞት ለዘመናት አስፈሪ ሆኖ የኖረ፡ ሁሉንም የሰው ዘር የተቆጣጠረ፡ መፍትሔም መድኃኒትም ያልተገኘለት፡ ነበር። አሁንም እንኳ መንግሥታት ስለሞት ለመነጋገር አጀንዳ ይዘው አያውቁም፡ ተመራማሪዎች የሞትን መድኃኒት ለመፈለግ ጥናት አድርገው አያውቁም። ሞት ሁሉንም ዝም ያሰኘ፡ ሁሉንም ጠቅልሎ የገዛ የምድራዊው ኑሮ የመጨረሻው ባለሥልጣን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ግን ሁሉ ተለወጠ። መድኃኒት ተገኘ፡፡ ለሞትም ሞት ታዘዘ። ይሄውም ትንሣኤ ነበረ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገው በሌላ በምንም ነገር ሳይሆን በሞቱ መሆኑ ያስገርማል። ሰው በቁሙ በሕይወት እያለ ብዙ ታላላቅ ነገሮችን ሊሠራ ይችላል። ከታመመ ምናልባት ጥቂት ነገሮችን ይሠራል። ከሞተ በኋላ ግን አንዳች ነገር ሊሠራ አይቻለውም። ሞት የሰው ልጆች የመጨረሻው ደካማ ባሕርይ፡ ምንም ሊሠራበት የማይችል ነው። አሁንም ሞት የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ የመጨረሻው ኃይለኛ ጉዳይ ነው። ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ኃያል የሆነውን ሞትን ድል ያደረገው በጣም ደካማ በሆነው ባሕርያችን በሞት ነው። እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በድካማችን ኃያሉን ጠላታችንን ሞትን ድል አደረገው።  «ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና»  ፩ቆሮ ፩፡፳፭።


 ኢየሱስ ክርስቶስ ባይነሳ ኖሮ ክርስትና ተረት ሆኖ ይቀር ነበር። አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ሰው ነበረ። ይህን አደረገ፡ በዚህ ወጣ በዚህ ወረደ፡ በመጨረሻ ሞተ፤ ተብሎ ያበቃ ነበር። ብዙ ታላላቅ ሰዎች መጨረሻቸው ሞተ፡ ተብሎ ተጠናቆአል። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፍጹም ሰው ቢሆንም ሞት ይዞ የሚያስቀረው ተራ ሰው ግን አልነበረም፤ አምላክም ነውና ሞቶ አልቀረም፡ ተነሳ። ስለዚህ የክርስቶስን ነገር እንደሌሎቹ «ነበረ» የምንለው ሳይሆን «አለ/ ነው» የምንለው ሕያው እውነት ነው። «ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።» ዕብ ፲፫፣፰። ትንሣኤው ለሕይወት ነውና ከትንሣኤ ቀጥሎ ሕይወት ነው። ሞት የለም ማለት ነው።
ልክ እንደክርስቶስ በስሙ የተጠሩት ክርስቲያኖች እርሱን ይመስሉታል ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ የተነሳው አንደኛ ለቤዛነት- ይሄም ሕይወትን ሊሰጠን፡ ሁለተኛ ለአርአያነት- ይሄም በኑሮ እንድንመስለው ነው።
በአርአያነት፡- በኑሮ ስንል ኑሮአችን ወይም አኗኗራችን እርሱን መምሰል አለበት ማለት ነው።
«የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። » ፩ጴጥ ፪፣፳፩።
« እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።» ፩ቆሮ ፲፩፣፩
ለምሳሌ በትሕትና፡ የደቀ መዛመርትን እግር እንዳጠበ እኛም እንዲሁ እንድናደርግ አዞናል።
« እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።» ዮሐ ፲፫፣፲፬-፲፭።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ሞቱ መላው ምድራዊ ሕይወቱ (ኑሮው) ልንከተለው የሚገባን ተግባራዊ ምሳሌ ነበር፡ በመጨረሻ በመስቀል ላይ በጭንቅ እና በመከራ ሆኖ እንኳ ለእርሱ በሚታሰብለት ሰዓት እርሱ ለሌሎች (ለእናቱ እና ለደቀ መዝሙሩ) ያስብ ነበረ። ዮሐ ፲፱፣፳፮-፳፯። እኛ ግን በመከራ ውስጥ አይደለም በድሎት ሆነን እንኳ ለራሳችን እንጂ ለሌሎች አናስብም። ግን የክርስቶስ የሆንን ክርስቲያኖች ነን እንላለን።
ኢየሱስ ክርስቶስን በየጊዜው ያሳደዱት በመጨረሻም ለሞት የዳረጉት የእግዚአብሔር ነን የሚሉት አይሁድ መሆናቸው የሚገርም ነው። ዛሬም በእውነት ክርስቶስን ያመኑ፡ ክርስቶስን የሚሰብኩ ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስበካቸው ስም እየተሰጣቸው በየቀኑ በሚደርስባቸው ስደት፡ ነቀፋ እና ስም ማጥፋት በመንፈሳቸው ስለሚጎዱ እንደተገደሉ ይቆጠራሉ። «ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። » ሮሜ ፰፣፴፮። ነገር ግን የትንሣኤው ኃይል ስላለ እንደገና በመንፈሳቸው ይነሣሉ። በክርስቶስ ምክንያት በየቀኑ የምንገደል ከሆነ በየቀኑ እየተነሳን ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ የትንሣኤው ነገር አንድ ሰሞን የሚዘከርና የሚያበቃ ጉዳይ ሳይሆን በዕለታዊ ኑሮአችን ትልቅ ስፍራ ያለው የሚያኖረን ኃይል ነው ማለት ነው።
በቤዛነት፡- ለሁሉም ሰው የሞተ ሁሉም አምነውበት ሕይወትን እንዲያገኙበት የተዘጋጀ የዓለም መድኃኒት ነው። እግዚአብሔርን ያላወቁ የጠፉት ወገኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ተብለዋል። ሙታን የተባሉትም ከእግዚአብሔር የተለዩ በመሆናቸው በመንፈሳቸው ስለሞቱ ነው። የጠፋው ልጅ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። «ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።» ሉቃ ፲፭፣፴፪ ።እንግዲህ ከእግዚአብሔር ተለይተው በመንፈስ የሞቱት እነዚህን ወገኖች ከሞቱበት ማንነት ሊያስነሳቸው የሚችለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰበክላቸው ብቻ ነው።  « «ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።» ኤፌ ፭፣፲፬።  እርሱ ከተሰበከላቸው የክርስቶስ የመነሳቱ እና የማስነሳቱ የትንሣኤው ኃይል  ለማያምኑት እንኳ ይሠራል።
በቤዛነቱ፡- ትንሣኤው በእርሱ ያመንን ሁሉ ሞተን እንደማንቀር እና እንደምንነሳ ተጨባጭ ማረጋገጫ (ምስክር) ነው። « ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤» ሮሜ ፮፣፭፤
በጸሎት ሃይማኖት መጨረሻ አንቀጽ «ወንሴፎ ትንሣኤ ሙታን ወሕይወተ ዘይመጽእ። - የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለን፤ የሚመጣውንም ሕይወት።» ልንል የቻልነው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ ብሎ በቃሉ ስላረጋገጠ፣ በተግባርም ሞቶ ስለተነሳ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነኝ አለ። ሙት የሚያስነሳ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሞቶ ስለተነሳም ጭምር ነው። ሙት ማስነሳት ለአገልጋዮቹም በጸጋ ሊሰጥ ይችላል፡ ሞቶ መነሳት ግን የእርሱ ብቻ ነው። በመጨረሻም ከሞት ማስነሳትም የእርሱ ብቻ ሥልጣን ነው። «ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።» ዮሐ ፮፣፵። ስለዚህ ሙት ስላስነሳ፡ ሞቶ ስለተነሳ፡ እና የሚሞቱትን በመጨረሻ ስለሚያስነሳ ትንሣኤ ነኝ አለ።
ቀጥሎ ሕይወት ነኝ አለ። ስለሕይወትነቱ በሌላም ቦታ እንዲህ ብሎአል  «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።» መንገድ መሄጃ ነው፤ እውነት መድረሻ ነው፤ ሕይወት በመጨረሻ የምንገባበት የዘላለም ሕይወት ነው። በየትኛውም ጉዞ የምንሄድበትን መድረሻ በትክክል ሊመራን፡ ሊያደርሰንም የሚችለው ከዚያው የሚኖር ቦታውን የሚያውቀው ብቻ ነው። ወደ አብ ሊያደርሰን የሚችለው ከአብ የመጣው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ከእርሱ በፊት የነበሩት ነቢያት፡ በኋላም የተከተሉት ሐዋርያት ሁሉም መንገዱ ያውና አሉ፤ ሰማያዊ አባቱ አብ «እርሱን ስሙት»፡ ምድራዊ እናቱ እመቤታችን « የሚላችሁን አድርጉ» ብለው ሁሉም ወደ እርሱ ያመለክታሉ፤ እርሱም እኔ.. ነኝ አለ። እኔ… ነኝ ካለ አበቃ፡ አይ አይደለህም ሊለው የሚችል ከቶ ማን ነው? ሌላም ተጨማሪ መንገድ.. ሕይወት አለ ማለትም አንችልም። ማረጋገጫ ወይም ምስክርም አያስፈልገንም። ማመን እና መቀበል ብቻ ነው።
«… ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።» ራእ ፩፣፭-፮።

5 comments:

  1. እግዚአብሄር ፍጻሜዎን ያሳምርልን፡፡ እድሜዎን ያርዝምልን

    ReplyDelete
  2. ....very excellent! but I have one question.'ቀጥሎ ሕይወት ነኝ አለ። ስለሕይወትነቱ በሌላም ቦታ እንዲህ ብሎአል «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።» መንገድ መሄጃ ነው፤ እውነት መድረሻ ነው፤ ሕይወት በመጨረሻ የምንገባበት የዘላለም ሕይወት ነው። በየትኛውም ጉዞ የምንሄድበትን መድረሻ በትክክል ሊመራን፡ ሊያደርሰንም የሚችለው ከዚያው የሚኖር ቦታውን የሚያውቀው ብቻ ነው። ወደ አብ ሊያደርሰን የሚችለው ከአብ የመጣው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ከእርሱ በፊት የነበሩት ነቢያት፡ በኋላም የተከተሉት ሐዋርያት ሁሉም መንገዱ ያውና አሉ፤ ሰማያዊ አባቱ አብ «እርሱን ስሙት»፡ ምድራዊ እናቱ እመቤታችን « የሚላችሁን አድርጉ» ብለው ሁሉም ወደ እርሱ ያመለክታሉ፤ እርሱም እኔ.. ነኝ አለ። እኔ… ነኝ ካለ አበቃ፡ አይ አይደለህም ሊለው የሚችል ከቶ ማን ነው? ሌላም ተጨማሪ መንገድ.. ሕይወት አለ ማለትም አንችልም። ማረጋገጫ ወይም ምስክርም አያስፈልገንም። ማመን እና መቀበል ብቻ ነው።' the above mentioned paragraph,does it have any relation with intercession? who is the intercessor? Jesus or Mary? I would appreciate in advance for your answer.

    ReplyDelete
  3. 10q for your comment. The mentioned paragraph doesn’t have any relation with intercession, as the Bible says Jesus is the One and the Only Savior, the way to reach the Father which means to be saved or enter into the Heaven.
    Neither is there salvation in any other: for there is none other name under heaven given among men, whereby we must be saved. Acts 4:12
    Clearly Jesus is the Savior, not the intercessor here, and at the end of the world He is the Judge.
    We are not talking about intercession here.

    ReplyDelete
  4. Tnx , I have a question. some people mentioned the sentence"እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።»as it is a proof Jesus is an intercessor whereas others refute this Jesus is Savior not an intercessor. Do you have any clear ideas about this? I would be grateful if you clearly answer me the first question. WHO IS THE INTERCESSOR? JESUS OR MARY?

    ReplyDelete
  5. I don’t worry about what people say about the verse. The commentary descended from our fathers put the meaning of the verse like this: refer to Commentary of John
    ዮሐ ፲፬፣ ቁ.፭፡ አቤቱ የምትሄድበትን አገር የማናውቅ መንገዱን እንደምን እናውቃለን አለው። አገሩ የታወቀ እንደሆነ የገሌ አገር መንገድ በየት በኩል ነው ተብሎ ተጠይቆ ይኬዳል።
    ቁ.፮ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ አነ ውእቱ ፎኖተ ጽድቅ ወሕይወት። የሕይወትና የጽድቅ መንገድ እኔ ነኝ ማለት ያንድነት የሦስትነት ባለቤት እኔ ነኝ። ወአልቦ ዘይመጽእ ኀበ አብ ዘእንበለ እንተ ኀቤየ። ያለኔ ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንም ተወላዲ ካላለ አብን ወላዲ የሚለው የለም።… ምንጭ፡-ወንጌል አንድምታ ንባቡና ትርጓሜው የኢትየጵያ ሊቃውንት እንደጻፉትና እንደተረጎሙት በተስፋ ገብረ-ሥላሴ የታተመ ፲፱፻፹፰ ዓ/ም።
    This means one should believe in Jesus as He is the Son of The Father, to be saved, The Base of Christianity.
    It is not my idea that should be asked, I think. It is what God says. And HE says so.
    Concerning your first question, I think I have answered it in my first comment. The mentioned paragraph doesn’t have any relation with intercession… We are not talking about intercession here Your question is completely out of the subject matter. The subject INTERCESSION is beyond the scope of this blog. There is no word INTERCESSOR in the blog or in the quoted verse. Why do the need arise to ask such question here?
    Perhaps we will mention it in the future and you will raise it then.
    We are here to study and discuss the BIBLE freely, aiming for life and love among people not for contentions or arguments.
    Thanks again for your replay and keep in touch.

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment