Friday, June 30, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፮


እግዚአብሔርን ፍለጋ - ቀጣይ
፫. የት ነው የምንፈልገው?

፫.፩ በተፈጥሮ፡-  ለእግዚአብሔር ሕልውና የመጀመሪያው ማስረጃ ሥነ ፍጥረት ነው።

የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤   ሮሜ ፩፣ ፳

እየመረመሩ ከተባለ - ለመመርመር ስሜት ህዋሳቶቻችንን እንጠቀማለን። ከእነዚህም አንዱ እና ዋናው ማየት ነው። ምን እናያለን? የምናየው ምንድን ነው?

ሀ. ፍጥረታት ከምን ተገኙ? ከየት መጡ?  የሚታየው ነገር ሁሉ አስገኚ አለው። በራሱ የተገኘ ነገር የለም።

o   አንዳንድ ወገኖች ዓለሙ የተገኘው እንዲሁ ነው የሚሉ አሉ፤ - ተመራማሪዎች።

§  በእግዚአብሔር መኖር የማያምን ጓደኛ የነበረው አንድ የእግዚአብሔር  ሰው  ያን ኢአማኒ ጓደኛውን «ዓለማት ከየት ተገኙ?» ሲለው

የማያምነው ጓደኛም፡- «እንዲሁ ተገኙ» ይለው ነበር።

አንድ ቀን አማኙ በካርቶን እና በወረቀት ቆንጆ ቤት ከሠራ በኋላ  ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው። በኋላ ከሃዲ ጓደኛው ሲመጣ የቤቱን ሞዴል አይቶ በጣም ተደነቀና ፡- « ከየት አገኘህው?» ሲለው - አማኙ  «እንዲሁ ተገኘ» አለው.. ይሄማ ሊሆን አይችልም  ሲል ያ አማኙ ጓደኛም፡- «አየህ እኔም ፍጥረታት ከየት ተገኙ? » ስልህ እንዲሁ ስትለኝ የነበረውም ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

§  የምናየው ነገር ሁሉ ሠሪ ወይም አስገኝ አለው። በራሱ የተገኘ ነገር የለም። ወንበሩ- አናጺ፣ ቤቱ-ግምበኛ… ሁሉም የየራሱ አስገኚ የሆነ ባለሙያ አለው። በአጠቃላይ የዚህ ውብ ተፈጥሮ አስገኝውስ ማን ነው?  ስንል -ፈጣሪ- እንዳለ /እንዳለው እንረዳለን።

. ፍጥረታት እንዴት ተገኙ?

o   አሁንም ተመራማሪዎች የመጀመሪያው ታላቅ ፍንዳታ (Big Bang) ከተከሰተ በኋላ- በሂደት ነገሮች ሁሉ ተገኙ፤ ይላሉ። ግን የመጀመሪያው የታላቅ ፍንዳታ ቁስ ከየት መጣ? ሲባል መልስ የለም።

ከዚያም በኋላ በአዝጋሚ ለውጥ- አንዱ ከአንዱ እየተወጣ.. ተገኙ ይላል።

o   አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፡-  ነገሮች አንዱ ከአንዱ ተገኘ ከተባለ ይህ ማለት እንግዲህ በከተማችን የምናያቸው ታላላቅ ፎቆች፣መንገዶች፣ ድልድዮች የተገኙት፡-  ጥሬ ዕቃዎቹ - ብረቱ፣ ሲሚንቶው ራሳቸውን አዘጋጅተው፣ እንጨቶች ራሳቸውን ጠርበው አስተካክልው፣ ጡቦች በራሳቸው እየተደረደሩ፣ ቆርቆሮው በራሱ እየተመታ፣ እየተጋጠመ ቤቱ ተሠራ የማለት ያህል ነው። ይህ ግን ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው።

o   ይህ ዓለም የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን በሥርዓት የተዋቀረ ዓለም ነው። Intelligent design - ግሩም ንድፍ ያረፈበት ድንቅ ተፈጥሮ ማለት ነው።

ሐ. ፍጥረታት እንዴት ይኖራሉ?

o   ፍጥረት ሁሉ በእንቅስቃሴ ላይ ነው። የፀሐይ መውጣት/መግባት - የምድር መዞር- የፕላኔቶች - .. ሁሉም በእንቅስቃሴ ላይ ነው። ማን ነው የሚያንቀሳቅሰው? ወይም ይህንን እንቅስቃሴ የሚመራው/ የሚቆጣጠረው ማን ነው?

§  ምድር፡- በፀሐይ ሥርዓት ውስጥ ፣ ወይም በሕዋ ውስጥ ያላት ሥፍራ ሕይወትን ሊያኖር በሚችል  መልኩ የተቀመጠች ናት። ምድር በፀሐይ ዙርያ ስትዞር ከምሕዋሯ  ትንሽ ራቅ ብትል - ሁሉም ነገር በረዶ ሆኖ በከፍተኛ ቅዝቃዜው ሕይወት በሙሉ ይሞታል፤  በተመሳሳይ ከምሕዋሯ ትንሽ ቀረብ ብትል በከፍተኛው ሙቀት የተነሳ ሁሉም ይቀልጥና ሕይወት አይኖርም፡።

§  ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ ወሳኝ የሆነው - ውኃ - በሶስቱም ኩነቶች የሚገኘው በምድር ብቻ ነው።  - / በጠጣርነት (በረዶ)፣ በፈሳሽነት (ውሃ) እና በእንፋሎት (ተን)/ ። ስለዚህ ከምድር ውጪ ሕይወት ያለው ነገር እስካሁን በሌሎች ዓለማት /ፕላኔቶች/ ማግኘት አልተቻለም።

፫.፪ በሕሊና፡-

§  በተፈጥሮ ሀሉም ሰው ክፉና ደጉን የመለየት ሚዛናዊነት ተቀምጦለታል።  ሰው ቢማርም ባይማርም፣ እግዚአብሔርን ቢያምንም ባያምንም በተፈጥሮው በሕሊናው መልካም ና መጥን የመለየት ችሎታ አለው። ይህ የሕሊና ዳኝነት - እንዴት በሁላችን ውስጥ ሊኖር ቻለ? ማን አስቀመጠው? - የጋራ ነገር እንዲኖረን ያደረገ አንድ አካል አለ?-- አዎ እርሱም የፈጠረን እግዚአብሔር ነው።

ü ሰው ሥጋ /matter/ ብቻ አይደለም መንፈስ /Spirit/ አለው። ቁሳዊ ነገር ከቁሳዊ ነገር ሊገኝ ይችላል። ነገር ግን መንፈሳዊ ነገር ከቁሳዊ ነገር ሊገኝ አይችልም። መንፈሳዊ ነገር ከመንፈስ /ከረቂቅ አካል/ ብቻ ነው ሊገኝ የሚችለው። -- እርሱም እግዚአብሔር ነው።

ü ስሜታዊ ነገሮች ፡ - ደስታ፣ ፍቅር፣ ሠላም፣ እምነት … የምንላቸው ማኅበራዊ እሴቶች ከቁሳዊ ነገር ሊገኙ አይችሉም። እነዚህን የማይዳሰሱ ረቂቅ ስሜቶችን ያስገኘ ስሜት ያለው / የሚሰማው/ ረቂቅ አካል ነው። -- እርሱም እግዚአብሔር ነው።

ü ፫.፫ በጠፈር ምርምር

እስከዛሬ ያልተደረሰባቸው ብዙ ፍጥረቶች ።

o   ስለከዋክብት ብዛት በሳይንሱ የሚሰጠውን መግለጫ ብናይ፡-

ü በዘመናዊ ግዙፍ የርቀት ማሳያ /ቴሌስኮኘ/ ተመርምሮ እንደተገኘው ከኛ ፀሐይ አካባቢ የሚገኙ ከዋክብት ቁጥራቸው እስከ ሀያ ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ያለመሣርያ በባዶ ዓይን ሲመለከቷቸው ግን አምስት ሺህ ብቻ ያህላሉ ይላሉ፡፡

ü ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት የከዋክብት ቁጥራቸው ሊወሰን የማይችል እልፍ አእላፍ /የብዙ ብዙ/ ስለሆነ የብዛታቸው ልክ እንኳንስ ተቆጥሮ ሊደረስበት ይቅርና ታይቶ የማያልቅ ነገር ሆኖባቸዋል፡፡ የርቀት መሣርያ መነጽሩን /ቴሌስኮኘ/ አሠራርና የማስተዋሉንም አኳኋን እያሻሻሉ በሄዱበት መጠን ቀድሞ ያልታዩ ሌሎች አዳዲስ ከዋክብት ይገኛሉ፡፡

ü የዚህን ሁኔታ ሲናገሩም መነጽሮቻችን ምንም ያህል ብናሻሽላቸው ከዋክብትን ጨርሰን ሙሉ በሙሉ ልናያቸው አንችልም፡፡ በጣም ዘልቀን ለማየት በቻልንበት መጠን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች አዳዲስ ከዋክብት ይወጣሉ፡፡ የእኛ ዕውቀት ከቶ ሊዘልቀው የማይቻል ነው ይላሉ፡፡ /የዕውቀት ብልጭ ፤ ከበደ ሚካኤል፡ ገጽ 158/

o   ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።  መዝ ፲፰/፲፱፣ ፩

የሰማይ ጥልቀት / የየከዋክብቱ ርቀት/፣-  አሁንም ለዚህ የሳይንሱን መግለጫዎች ብናይ፡-

ü በፀሐይና በመሬት መካከል ያለው ርቀት ወደ 150 ሚሊዮን ኪ.ሜ ይጠጋል፡፡ የርቀቱን ግምት ለመገንዘብ በመድፍ ጥይት ጉዞ መስለው ይናገራሉ፡፡ የመድፍ ጥይት ፍጥነቱን ሳይቀንስ ከምድር ወደ ፀሐይ ቢተኮስ ከፀሐይ ለመድረስ 20 ዓመት ይፈጅበታል፡፡ ይህም ፀሐይ ከመሬት ምን ያህል በጣም የራቀች መሆኗን ያሳየናል፡፡

ü በማታ ከምናያቸው ስፍር ቁጥር ከሌላቸው በርካታ ከዋክብት ውስጥ ለመሬት ቅርብ የሆነችው ኮከብ  ከላይ በተቀመጠው ምሳሌ መሠረት ርቀቷ እጅግ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ የመድፍ ጥይቱ ወደዚች ኮከብ ቢተኮስ ከርሷ ለመድረስ 7 ሺህ ዓመ ት ይወስድበታል፡፡

ü በዚህ ልኬታ የሌሎችን ከዋክብት ርቀት ብናስብ ምን ያህል የማይደረስበት እንደሚሆን መገመት እንችላለን፡፡ በየከዋክብቱ መሀል ያለው ርቀትም እጅግ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የሚለካው ብርሃን ከነርሱ ለመድረስ በሚፈጅበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም የብርሃን ዓመት ይባላል። ….

እግዚአብሔር በሰጠን አእምሮ - እየተመራመርን- ይሄን ሁሉ ስናይ /ስንሰማ/ የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ ምን ያህል ግሩም ድንቅ ነው እንድል ያደርገናል።

ü ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ የሆኑ በሳይንስ ሊረጋገጡ /ሊመለሱ ያልቻሉ ብዙ ጉዳዮች /ክስተቶች አሉ።

o   የአጋንንት እና የመናፍስት አሠራር ፤ ተአምራት፣ ድንቆች….

o   የነፍስ ምንነት፣ ሞት ምንድን ነው? ወዘተ…

እነዚህ ሁሉ የሚያሳየን ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉን የሚቆጣጠር እና የሚመራ አምላክ እንዳለ ነው።   ታዲያ የእግዚአብሔርን መኖር በተፈጥሮ፣ በሕሊና ፣ በመሳሰሉት… ካረጋገጥን በኋላ የምንፈልገው ምኑን ነው?

... /ይቀጥላል/
ዲ/ን ኢንጅነር አብርሃም አብደላ
ጎንደር - ሰኔ ፳፫፣ ፳፻፱ ዓ/ም

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment