Thursday, June 8, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፭


እግዚአብሔርን ፍለጋ


ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።

ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።   የሐዋ ፲፯፣ ፳፮ - ፳፰

፩. እግዚአብሔርን መፈለግ ለምን አስፈለገ?

ü ተፈጠርንበት ዋና ዓላማ በመሆኑ-  እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፡-

·        የሰውን ወገኖች ከአንድ ፈጠረ - ከአዳምና ከሔዋን። አንድ ጊዜ ፈጠረ፣ በኋላ ብዙ ተባዙ ባለው አምላካዊ ቃል  በመዋለድ የሰው ዘር ይቀጥላል።  

o   …..እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥  ዘፍ ፩፡ ፳፯ - ፳፰

o   አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። ዘፍ ፫፣ ፳

·        የምንኖርበትን ዘመን - እና - ስፍራ /ቦታ/ መደበልን።  በየት ዘመን እስከ ስንት ጊዜ፣ በየት ሃገር ከየትኛው ቤተሰብ እንደምንወለድ እድሜና ሥፍራ የመደበልን እግዚአብሔር ነው።

ስለዚህ «አፄ /አቶ እገሌ ያለዘመናቸው የተወለዱ… »  የምንለው ፈጽሞ ስህተት ነው ማለት ነው። 

·        እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት ዓላማ እንዲፈልገው  ነው። በሰጠው ነጻነት ተጠቅሞ ፈልጎ፣ አግኝቶ ፣ ወዶ እንዲከተለው እና አብሮት እንዲኖር።

·        እግዚአብሔርን ስለመፈለግ ዳዊት እንዲህ ብሏል፡-

·        …. በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።

እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።  መዝ ፻፬/፻፭፣ ፩ - ፬
እግዚአብሔርን የምንፈልገው ለምንድን ነው? ከላይ በጥቅሱ እንዳየነው፡-

 

ü ልብን ደስ ስለሚያሰኝ፣-  እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው

o   ዘላቂ እና ከውስጥ - ከልብ - የሆነ እውነተኛ ደስታ ያለው እግዚአብሔርን በመፈለግ ነው። በሌላም ቦታ እንዲህ ተብሏል፡-

§  ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵ ፬፣ ፬

ü ለመጽናት፣-   እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፡

o   አንድ ሰው በተቸገረ ጊዜ - እገሌን ነው የምፈልግ እርሱ ይምጣልኝ - ይላል።

በፈተና በሕይወት ውጣ ውረድ ለመጽናት የሚረዳን የሚያስፈልገን እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ü ለሚፈልጉት ምላሽ ስለሚሰጥ፣-  እግዚአብሔር እርሱን ለሚፈልጉት ምላሽ ይሰጣል እንጂ ተደብቆ አይቀመጥም።

   ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።  ዕብ ፲፩፣ ፮

o   በፍለጋ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ ሁለት ነገር ማመን አለበት፡

§  ፩. እግዚአብሔር እንዳለ - እግዚአብሔር አለ።

§  ፪. ለሚፈልጉትም ዋጋ ይሰጣል። - ይመልሳል። ይገናኛል።

-      ፈልጉት ስንባል ሩቅ  ወይም ረቂቅ ስለሆነ ግን አይደለም። ምክንያቱም  - ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።  ተብሏልና፤ ስለዚህ  ቅርብ ነው።

-      በምናየው በተፈጥሮ፣ ዓለምን በማስተዳደሩ /በመግቦቱ/ ፣ በነፍሳችን ጥማት… እግዚአብሔርን መፈለግ ግድ ይላል። እግዚአብሔር የራቀ / ሩቅ/ የሚሆነው ዓይነ-ልቦናችን በኃጢአት ጨለማ ሲያዝ ብቻ ነው።

-      ማንም ሰው ከአምልኮ ውጪ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር / ከአምላክ/ ፍለጋ ተለይቶ አያውቅም። ሁሉም ሰው የሚታመንበት፣ ተስፋ የሚያደርገው፣ አንድ አካል ይፈልጋል። እግዚአብሔርን የማያውቁና የማያምኑ ሰዎች እንኳን -ጨርሶ እምነት የለሽ- አይደሉም። የሚታመኑበት ይለያይ እንደሆነ እንጂ  የሆነ አንድ የሚታመኑበት ነገር አላቸው፤ - ጣኦት፣ ሃብት፣ ….

-      እግዚአብሔርን ፍለጋ አስፈላጊነቱ /አንገብጋቢነቱ/- በጨለማ ውስጥ መብራት የመፈለግ ያህል ነው። ካለዚያ የሚታይ ነገር አይኖርም፣ የሕይወት ጉዞው መደናበር ነው የሚሆነው። ሕይወት ያለእግዚአብሔር ጨለማ ናት።

እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት። ፩ ዮሐ ፩፣ ፭

፪. እግዚአብሔርን እንዴት ነው የምንፈልገው?

ü በአእምሮ፡- /በዕውቀት/ -  ምናልባትም እየመረመሩ

o   ምናልባት ለምን ተባለ? በተሰጠን አእምሮና ነጻ ፈቃድ በምናደርገው ምርምር እግዚአብሔርን ላንደርስበት እንችላለን። በዓለማዊ ጥበብና ምርምር ብቻ እግዚአብሔርን ማግኘት አይቻልም።

 በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።  ፩ ቆሮ ፩፣ ፳፩።

o   ሰው ከተፈጠረ በኋላ የሚያውቀው እግዘአብሔር የፈጠረውን መልካም ብቻ ነበር፤ የተከለከለችውን -በተለምዶ ዕጸ-በለስ - ዛፍን ከበላ በኋላ ክፉንም አወቀ፤ ለዚህ ነው ዛፊቱ፡- «፣መልካምና ክፉን የምታሳውቅ ዛፍ»  የተባለች። ከውድቀት በኋላ ሰው በተሰጠው አእምሮ በዘመናት ሁሉ እውቀቱን በማሳደጉ ወደ እነዚህ ሁለት ጎራዎች ሄዷል፡- ወደ መልካምና ወደ ክፉ።

§  መልካም ውጤት - ምድርን ለኑሮ አመቺ ማደረጋችን - መጓጓዣ፣ መኖሪያ…ማሻሻላችን.

§  ክፉ ውጤት - ሰው ሰራሽ የጥፋት ስጋቶች መፈጠራቸው፡- ጠመንጃ፣ መርዝ….መሥራታችን

ስለዚህ አዳም /ሰው/  መልካሙንና ክፉን  የምታስታውቀውን ዛፍ ስለበላ እና ስላወቀ - ያወቀውን መተግበር ጀመር።

o   የተሰጠን አእምሮ ዋናው ዓላማ በተፈጠርንበት መልካምነት፣ መልካም የሆነውን ፍጥረት በማስተዳደር ፣መልካም የሆነውን እግዚአብሔርን በመፈለግና /በመምረጥ/ ለማምለክ ነበረ።

o   ፍለጋውን ማስቆም አይቻልም፤ ሰው ወደደም ጠላም በፍለጋ ውስጥ ነው።

ዓይን እስካለ አላይም ማለት አይቻልም፤ እግርም እስካለ አልሄድም ማለት አይቻልም።

o   ፍለጋው ወደ እግዚአብሔር ሊያደርሰን ይችላል፣ ከእግዚአብሔር ሊያርቀንም ይችላል። እንደ ምንሄድበት አቅጣጫ ይወሰናል።

o   ስለዚህ በሕይወት ጉዞ ላይ- በነገሮች ፍለጋ ዋናው ቁምነገር  ዝምብሎ መሄዳችን /መኖራችን/ ሳይሆን ወዴት እየሄድን ነው?  የሚለው ነው። ዋናው አቅጣጫው ነው።

 ግን እግዚአብሔርን የምንፈልገው የት ነው?....... ይቀጥላል።
------------ይቆየን-------------------
ዲ/ን ኢንጅነር አብርሃም አብደላ
ሰኔ ፩፣ ፳፻፱ ዓ/ም
ጎንደር

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment