Wednesday, May 17, 2017

እግዚአብሔርን ማወቅ - ክፍል ፬


ችሎታዊ  መገለጫዎቹ፡-

፩. ሁሉን ቻይ /ከሃሊ ኩሉ - ኤልሻዳይ/፡- የሚሳነው ነገር የለም። ዘፍ ፲፰፣ ፲፬

o   በእግዚአብሔር ዘንድ «አይቻልም» የሚባል ነገር  የለም።
ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው፤ ፪ ነገ ፫፣ ፲፰ እንደተባለው።

o   እግዚአብሔር ነገሮችን የማያደርጋቸው ወይም የሚያዘገያቸው ስላልቻለ ሳይሆን ስላልፈለገ ወይም ጊዜያቸው ስላልሆነ ነው።

o   ስናጠፋ ወዲያው የማይቀጣን እንድንመለስ ጊዜ እየሰጠን ነው።

ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። ፪ ጴጥ ፫፣፱

ሁሉን ቻይ እና ታጋሽ የሆነውን የእግዚአብሔርን ነገር፡-

-      «…አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።

-      ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።…»   ኢሳ ፵፣ ፳፯ - ፴፩

፪. ሁሉን አዋቂ ፡- ከእርሱ እውቅናና ውጪ የሆነ/ሊሆን የሚችል ነገር ፈጽሞ የለም።

-      « የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? »  ሮሜ ፲፩፣ ፴፫ - ፴፭

-      በሁሉም ቦታ ያለ ሁሉን ነገር በአንድ ጊዜ ነው የሚያውቀው፣ --  ማካሪ የለውም።

ሞራላዊ መገለጫዎቹ፡  ከሰው ባሕርያት ጋር በሚነጻጸር መልኩ ስንገልጸው፡- እግዚአብሔር፡-


ቅዱስ ነው፣-  ልዩ ነው፤ የሚመስለው የለም ማለት ነው። - ከኃጢአት ጋር ሊስማማ/ሊኖር አይችልም። ለዘላለም ከኃጢአት የተለየ ነው፤

ጻድቅ ነው፡- ፍትሐዊ ባሕርይውን ያሳያል። ጥፋትን አይቶ አያልፍም፤ ይቀጣል።

ፍቅር ነው፡-   ፍቅር የሚለውን ቃል አባቶች በየፊደሉ ሲተረጉሙት፡-

ፍ፡- ፍጹም፣ ቅ፡- ቅዱስ፣ ር፡- ርህሩህ.. ስለዚህ ፍጹም፣ ቅዱስ፣ ርህሩህ የሆነ ፫ቱንም ያሟላ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ፡- እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፡- ፩ ዮሐ ፬፣ ፲፮

ይህንን በምሥጢረ-ሥላሴ በመጠኑ ለማሳየት ያህል፡-

እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው፣ ሦስትነቱ በስም፣ በአካል፣ በግብር ነው።

አብ፡- ለሥላሴ ልባቸው ነው፣ የአሳብ መነሻ

ወልድ፡- ለሥላሴ ቃላቸው ነው፣ መናገሪያ

መንፈስ ቅዱስ፡- ለሥላሴ ሕይወታቸው ነው፣ መኖሪያ

የአብ ልብ የአብ ብቻ አይደለም፤ የወልድም የመንፈስ ቅዱስም ነው እንጂ፤

የወልድ ቃል የወልድ ብቻ አይደለም፤ የአብም የመንፈስ ቅዱስም ነው እንጂ፤

የመንፈስ ቅዱስ ሕይወት የመንፈስ ቅዱስ ብቻ አይደለም፤ የአብም የወልድም ነው እንጂ።

በሥላሴ ዘንድ የእኔ ብቻ የሚባል የለም፤ የአንዱ የሌላውም ነው። ይህ የማይመረመር ፍጹም ፍቅር እግዚአብሔርን ፍቅር አሰኝቶታል።

ጥበበኛ ነው፡-  የሚያደርገው ሁሉ እንከን/ ጉድለት የለበትም። ሁሉንም ነገር በጊዜው በጥሩ ሁኔታ ለተሻለ ዓላማ ያደርጋል።

 « ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው»  መክ ፫፣ ፲፩

n  በዓለም ላይ ስንኖር እጅግ ጠቃሚና ወሳኙ ጉዳይ ምንድን ነው? ቢባል - እግዚአብሔርን ማወቅ, ነው፤ የሁሉም ነገር እና ጥያቄ መሠረታዊ መልስ ያለው በዚህ ውስጥ ነው።

« አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤»  ፊልጵ ፫፣ ፰

እግዚአብሔርን / ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ -ለእርሱ ያለን ዕውቀት- ከሌላው ነገር ሁሉ ጋር ሲነጻጸር ጉዳት ማለት ነው።

n  እግዚአብሔርን ለማወቅ እርሱ ራሱን በሰው - በሚገባን የራሳችን ባሕርይ - የገለጠልን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ ክርስቶስን ስናውቅ እግዚአብሔርን እናውቃለን ማለት ነው።

n  ሙሉ በሙሉ አውቀን ባንጨርሰውም - እርሱን እያወቅን ፡ ስለእርሱ ያለን እውቀት እየጨመረ  ይሄዳል። ባወቅነው መጠንም ከእርሱ ጋር ያለን ቀረቤታ/ግንኙነት/ እየጨመረ ይሄዳል።

n  ስለእርሱ ያለን እውቀት ሙሉ የሚሆነው በሰማያዊ መንግሥት በዘላለማዊ ሕይወት ከእርሱ ጋር ሰንኖር ነው።

n  እኛ ብዙ ጊዜ የምንፈልገው እግዚአብሔርን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ነው። አንድ መምህር እንዳለው፡- « ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ ብዙ ጊዜ ፊቱን ሳይሆን እጁን እንፈልጋለን።»

o   …በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።

       እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።… መዝ ፻፬/፻፭፣ ፫-፬

እርሱን ራሱን ሳይሆን የሚሰጠንን እንፈልጋለን- የሚሰጠን ግን በዚች ምድር የሚቀር ነው። ዘላለም አብረን የምንኖረው ከራሱ ጋር ነው።

n  የሱስ ክርስቶስ የሚሰጠው የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔርን ማወቅ ስለሆነ ነው።

እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።  ዮሐ ፲፯፣ ፫

የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔርን ቀጥሎም ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።

የመረጃ ሳይሆን የሕይወት እውቀት፣ የግንኙነት፣ የልምምድ እውቀት… ማለት ነው፡

--ምን እንደምንፈልግ ሳናውቅ ወደ ፍለጋ አንባም፡- የምንፈልገውን ነገር አውቀን ነው ወደ ፍለጋ የምንገባው። ስናገኘው እንድንረዳው።

እግዚአብሔርን ማወቅ - እግዚአብሔርን እንድንፈልግ ያደርገናል።

በቀጣይ - እግዚአብሔርን ፍለጋ / የፈጣሪ መኖር/ እናያለን።

ይቆየን።
አብርሃም አብደላ (ዲያቆን ኢንጅነር)
ግንቦት ፱/ ፳፻፱ ዓ/ም - 09/09/09 
ጎንደር

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment