Friday, October 19, 2012

ብሉይ ኪዳን - የኦሪት ክፍል


በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተከታታይ ትምህርታችን ባለፉት ጊዜያት ለጥናታችን የሚያስፈልጉንን ነጥቦች ካየን በኋላ ለአጠቃላይ ግንዛቤ የብሉይ ኪዳንን እና የአዲስ ኪዳንን ጠቅለል ያለ ታሪካዊ ዳሰሳ ተመልከተናል። በቀጣይ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱ ኪዳናት በተከፋፈሉባቸው ሥነ-ጽሑፋዊ ይዘት ቅደም ተከተል መሠረት እያንዳንዳቸውን በየተራ እንመለከታለን።
ብሉይ ኪዳን በሥነ-ጽሑፋዊ ይዘቱ በአራት እንደሚከፈል ቀደም ብለን ተመልክተናል። እነዚህም፡
፩. ሕግ፡ - ከኦሪት ዘፍጥረት - ኦሪት ዘዳግም --- ፭ መጻሕፍት
፪. ታሪክ ፡- ከመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ- መጽሐፈ አስቴር-- ፲፪ መጻሕፍት
፫. ጥበብ፡-  ከመጽሐፈ ኢዮብ- መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን-- ፭ መጻሕፍት
፬. ትንቢት፡- ከትንቢተ ኢሳይያስ - ትንቢተ ሚልክያስ---፲፯ መጻሕፍት ናቸው።
ለዛሬ የሕግ ክፍል የሆነውን አምስቱን የኦሪት መጻሕፍት ጠቅለል አድርገን እናያለን።
ኦሪት የሚለው ቃል አራይታ ከሚለው የጥንት የሶርያ ቋንቋ እንደተገኘ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይናገራል። ትርጉሙም ሕግ፣ ትምህርት ማለት ነው። ይህም ሕግ ወይም ትእዛዝ ከእብራይስጡ ቶራህ ከሚለው ቃል እንደተገኘም ምሁራን ይናገራሉ። የሕግ ክፍል የተባለው የኦሪት መጻሕፍት ኦሪት ዘፍጥረት፣ ኦሪት ዘጸአት፣ ኦሪት ዘሌዋውያን፣ ኦሪት ዘኊልቁ እና ኦሪት ዘዳግም የተባሉትን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት ያጠቃልላል። አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት ፔንታቱክ በመባልም ይታወቃሉ። አሁን ድረስ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ዋና መጻሕፍቶቻቸው እንደሆኑ ይነገራል።
አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት በአብዛኛው የተለያዩ ነገሮችን አጀማመር ይገልጹልናል። ከእነዚህም፡-
የፍጥረትን አጀማመር -የሰማይን የምድርን እና በውስጡ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ጅማሬ፣
በአዳምና በሔዋን መፈጠር መላው የሰው ዘር እንዴት እንደተባዛ እና ምድርን እየሞላ እንደሄደ፣
ኃጢአት እንዴት ወደዓለም እንደገባ እና ሰው እግዚአብሔርን ማምለክ እንዴት እንደተወ፣
እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ከኖኅ፣ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን እንደጀመረ፣
በብሉይ ኪዳን ዋና የታሪክ ባለቤት የሆኑት የእስራኤል ሕዝብ አመጣጥ እንዴት እንደተጀመረ፣
የተጻፈ ሕግ፣ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት ሊጠብቃቸው የሚገቡ በርካታ ሥርዓቶች…. ወዘተ አጀማመር ይገልጻል።
በኦሪት መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያደረገለትን እንክብካቤ እና ትድግና፡ ሕዝቡም ለእግዚአብሔር ሊፈጽሙ የሚገባቸውን ሥርዓትና ቅድስና ይዘረዝራል። የተሰጡት ሕግና ሥርዓቶች በጣም በርካታ፡ በዝርዝር እና ሁለመናቸውን የሚመለከት ነበረ። በሁለንተናቸው አምላካቸውን በቅድስና እንዲመስሉ ለእርሱ የተለየ ሕዝብ እንዲሆኑ ስለእያንዳንዱ የሕይወት ክፍላቸው በዝርዝር እና በጥልቅ ተነግሯቸዋል። አብዛኛው የኦሪት ክፍል ለጊዜው አሰልቺ የሚመስል በኋላ ግን ጠቃሚነቱ የሚጎላ በበርካታ ዝርዝር ሕግጋትና ሥርዓት የተሞላ ታሪካዊ ፍሰት ያለው ክፍል ነው።


በኦሪት ዘፍጥረት ከምዕራፍ ፩ እስከ ፲፩ ስለመላው ሰው /ዓለም ይናገርና ከምዕራፍ ፲፪ በኋላ ግን በቀረው ክፍል ስለእስራኤላውያን አባቶች አነሳስ፣ ዘራቸው ወደ ግብጽ መውረድ፡ ታላቅ ሕዝብ ሆነው በዝተው በታላቅ ተአምራት በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት ነጻ መውጣታቸው፡ በበረሃ በጉዞአቸው ባለመታዘዛቸው የደረሰባቸውን መንከራተት፣ ሕጉንና ሥርዓቱን መቀበላቸውን በመጨረሻም ቃል የተገባላቸውን ምድረ ርስት ለመውረስ ዝግጅታቸውን አጠናቀው እንደተቃረቡ በዝርዝር ይናገራል።
የመላው መጽሐፍ ቅዱስ የታሪኩ ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነ ቢታወቅም በዚህ በኦሪት ክፍል ውስጥ ዋና የታሪኩ ተዋናይ ሙሴ ነበረ። ምንም እንኳ የሙሴ ታሪክ ከሁለተኛው መጽሐፍ ከኦሪት ዘጸአት ቢጀምርም እስራኤልን ከግብጽ እንዲወጡ በማድረግ፣ በምድረ-በዳ በተንከራተቱ ጊዜ አብሯቸው በመሆንና በማበረታታት እስከ ከነዓን በማቅረብ ትልቅ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ ያገለገለ፡ ሰፊውን የእስራኤላውያንን ሕይወት በመለወጥ በራእይ እንዲጓዙ ያደረገ ታላቅ መሪ ነበረ። በዚህ ምክንያት እንዲሁም መጻሕፍቱን እርሱ እንደጻፋቸው ስለሚታመን እነዚህ የኦሪት/የሕግ መጻሕፍት የሙሴ መጻሕፍት ተብለው ይጠቀሳሉ።
አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት በሙሴ እንደተጻፉ የሚገልጹ ማስረጃዎች አሉ።
«እንዲህም ሆነ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች በመጽሐፍ ከጻፈ ከፈጸመም በኋላ፥  ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ… »  ዘዳ ፴፬፣፳፩።
« መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን።» ማር ፲፪፣፲፱።
« ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና።» ሮሜ ፲፣፭።
ሙሴ እስራኤለውያንን ከግብጽ ባርነት ለማውጣት እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብ የተጠቀመበት ስልት መዳረሻቸውን ወይም የመጨረሻውን ግብ ብቻ እንዲመለከቱ ማድረጉ ነበረ። በዚህም የተነሳ በዓለማውያን ምሁራን ዘንድ BPR – Business Process Reengineering - የመሠረታዊ ሂደት ለውጥ- በአመራር ትምህርት ውስጥ ስለራእይ/ግብ ሙሴ ግንባር ቀደም ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል።
ሙሴ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆነውን ሕዝብ (እስከ ሁለት ሚሊየን የሚሉም አሉ) ከግብጽ ይዞ ሲወጣ በመንገድ ምን ይበላል፤ ምን ይጠጣል የሚል ስጋት ሳይኖርበት በእግዚአብሔርና በተናገረው ቃሉ ታምኖ ወጣ። « ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ፥ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ።» ዕብ ፫፣፪።
እግዚአብሔርም በሙሴ በኩል ሕዝቡ በጉዟቸው የሚገጥማቸውን አልነገራቸውም። ውኃ ጥሙን፣ በረሃውን፣ መንከራተቱን… አልተናገረም፤ ከዚህ ሁሉ እንደሚያድናቸው ያውቃልና የመጨረሻውን ግባቸውን እንዲያዩ፣ ያንም እያዩ በተስፋ እንዲጓዙ ተናገራቸው፡፡
ሙሴ በጠንካራ መሪነቱ ለሕዝቡ ራሱን ለመስዋዕት ለማቅረብ የተዘጋጀ ነበረ። በሕዝቡ መንፈሳዊ ዝለትና ኃጢአት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ሊያጠፋቸው በፈለገ ጊዜ ሙሴ ራሱን ለመስዋዕት በሚያዘጋጅ ቃል ለሕዝቡ ምልጃን አቅርቧል።
« ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፦ ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤
አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ።» ዘጸ ፴፪፣፴፩-፴፪።
በዚህም ሥራው ሙሴ እንደእሱ ያለ ትሑት በምድር እንደሌለ በሌላ ቦታ ተመሰከረለት።
« ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።» ዘኁ ፲፫፣፫
ይሁን እንጂ ሙሴ ሰው እንደመሆኑ መጠን ፍጹም አልነበረምና ከነበረበት ድካም አንዱ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሰጠውን ክብር ለራሱና ለአሮን በማጋራት ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ መናገሩ ነው። በዚህም ምክንያት ከነዓን ምድረ-ርስት ሳይገባ ቀርቷል።
« ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው። እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው። ….
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን፦ በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው። » ዘኁ ፳፣፲-፲፪።
በአጠቃላይ የኦሪት ክፍል ከነገሮች ጅማሬ ጋር እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ከግብጽ እስከ ከነዓን መግቢያ ድረስ ባደረገው ጉዞ የደረሰበትን ነገር፣ የተቀበሉአቸውን ሕግጋት ወዘተ… የሚዘረዝር የእስራኤላውያን ሕዝብ ታሪክ ነው። ይህ በሙሴ ዋና ተዋናይነት የሚተረከው የብሉይ ኪዳን የመጀመሪያ ክፍል ከዘፍጥረት - ዘዳግም ወጥነትና ተከታታይነተ ያለው የመላው መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መግቢያ እና የነገሮች ሁሉ መነሻ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖንም በቀጣይ የብሉይ ኪዳንን ሁለተኛ ክፍል የሆነውን የታሪክ ክፍል እናያለን።
ይቆየን። 

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment