ባለፈው ጥናታችን መጽሐፍ ቅዱስ
በሥነ-ጽሑፋዊ ይዘቱ ሁለቱ ኪዳናት በሚከፋፈሉበት መሠረት የብሉይ ኪዳንን የኦሪት ክፍል ጠቅለል አድርገን ማየታችን ይታወሳል። እነዚህም
አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት የሆኑት ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትንና የባለታሪኩ ዋና ተዋናይ የሆኑትን እስራኤላውያንንና መሪያቸውን
ሙሴን ተመልክተናል። ባለፈው ያላየነው ነጥብ ይህ የኦሪት ክፍል የተፈጸመበት ዘመን 4000 ዓመት ገደማ መሆኑን ነው። ይህም ማለት
ከብሉይ ኪዳን 5500 ዘመን ውስጥ 4000 የሚሆነው ዘመን ከዓለም መፈጠር አንስቶ እስራኤላውያን ከነዓንን ለመውረስ እስከተቃረቡበት
ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። በሚገርም ሁኔታ ከዚህ ውስጥ ከአዳም - አብርሃም ከዘፍ ፩ - ፲፩ ያለው ዘመን የ3500 ዓመት የዓለም ታሪክ መሆኑ ነው። ከአብርሃም እስከ ሙሴ ደግሞ ወደ 500
ዓመት ገደማ ሲሆን ከሙሴ በኋላ የቀረው የብሉይ ኪዳን ታሪክ የተፈጸመው በቀሪው 1500 ዘመን ነው። በሌላ አገላለጽ ሙሴ የተነሳው
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500 ዓመት ገደማ ነው። ስለዘመናቱ ይህን ያህል ካስታወስን ለዛሬ ከብሉይ ኪዳን ሁለተኛው የሆነውን
የታሪክን ክፍል እንመልከት።
የታሪክ ክፍል የሚባሉት ከመጽሐፈ
ኢያሱ ወልደ ነዌ እስከ መጽሐፈ አስቴር ያሉት አስራ ሁለት መጻሕፍት ሲሆኑ እነርሱም መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ፣ መጽሐፈ መሳፍንት፣
መጽሐፈ ሩት፣ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልእ፣ መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልእ፣ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልእ፣ መጽሐፈ
ዕዝራ፣ መጽሐፈ ነህምያ እና መጽሐፈ አስቴር ናቸው። እነዚህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1500 እስከ 400 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ
የተፈጸሙ እንደሆኑ ይነገራል። ቀሪው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ የሚካተቱት በዚሁ ዘመን ውስጥ ነው። ከብሉይ ኪዳን ሦስተኛ ና
አራተኛ ክፍል የሆኑት የጥበብ እና የትንቢት መጻሕፍት የተጻፉት በዚህ የእስራኤላውያን የታረክ ዘመን ውስጥ ነው። ምንም እንኳ በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ የጥበብ/የቅኔ እና የትንቢት መጻሕፍት ከታሪክ ክፍል ቀጥለው ለብቻ ተጠርዘው ቢገኙም የዳዊት የሰሎሞን.. መዝሙራት፣
የኢሳይያስ፣ ኤርምያስ… ትንቢቶች ሁሉ የተጻፉት/የተነገሩት በዚህ በታሪክ ክፍል ውስጥ ነው።
እንግዲህ የታሪክ ክፍል የብሉይ
ኪዳን የታሪክ ባለቤት የሆኑት የእስራኤላውያን ቀጣይ ታሪክ ነው። ይህም ማለት ከግብጽ ወጥተው ከነዓንን ለመውረስ ከተቃረቡበት ከኦሪት
ክፍል መጨረሻ ከዘዳግም በመቀጠል በኢያሱ ከነዓንን ከወረሱ በኋላ ለምርኮ ወደ በባቢሎን እስከ ተወሰዱበት እስከ አስቴር ዘመን ድረስ
ያለውን ቀሪ ታሪካቸውን ይተርካል።
እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በሙሴ
በኩል ምድረ-ርስትን ለማውረስ የገባላቸውን ቃል ኪዳን እንዴት እንደፈጸመ በዚህ ክፍል እናያለን። እግዚአብሔር እስራኤላውያን ከግብጽ
ሲነሱ እንደሚያወርሳቸው በተናገረው መሠረት ቃሉን ሳያጥፍ በኢያሱ መሪነት ከነዓንን አውርሷቸዋል። ከዚያም በኋላ ራሳቸውን የቻሉ
መንግሥት ይሆኑ ዘንድ በጠየቁት መሠረት እንደ ሳኦል፣ ዳዊት.. የመሳሰሉት ነገሥታትን በማስነሳት፣ ጠላቶቻቸውምንም ድል በማድረግ
ሲንከባከባቸው ቆይቷል። ይሁን እንጂ እስራኤል በቀረው ኑሮአቸው በእነርሱ በኩል ቃል ኪዳኑን ለማክበር የገቡትን ትእዛዛቱን የመጠበቁን
ነገር ችላ በማለታቸውና ሕግጋቱን በመጣስ በኃጢአት በመውደቃቸው እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ እንዴት እንደቀጣቸው ክፍሉ ያሳያየናል።
በጠላቶቻቸው ድል ሲሆኑ፣ ከሰሎሞን በኋላ መንግሥታቸው ለሁለት ሲከፈል፣ በምርኮ እንደተወሰዱና ከምድራቸው እንደተፈናቀሉ… እናያለን።
በኋላም በእነ እዝራ ከምርኮ ወደ ሃገራቸው በመመለስ እንደገና ቤተ መቅደስን ሰርተው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመጠኑም
ቢሆን አድሰዋል።
በቅደም ተከተላቸው ይህንን የእስራኤላውያንን
ታሪክ ጠቅለል አድርገን ስናይ፡-
በመጽሐፈ ኢያሱ - እስራኤላውያን
ቃል የተገባላቸውን ከነዓንን ዙርያዋን በመክበብ የሚኖሩባትን አሕዛብ ድል ካደረጉ በኋላ ምድሪቱን እንደወረሱ እና በየነገዳቸው ርስትን
እንደተከፋፈሉ ይናገራል።
በመጽሐፈ መሳፍንት እና ሩት -
ምድሪቱን ከወረሱ በኋላ በተለያዩ መሳፍንት /አስተዳዳሪዎች/ እንደቆዩና ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው በተለያየ ጊዜ በጠላቶቻቸው
ይጠቁ እንደነበረ ያሳየናል።
በ፩ኛ እና ፪ኛ ሳሙኤል እስከ ፩ኛ
ነገሥት አጋማሽ - እስራኤላውያን በወረሷት ምድር ተጠናክረው እንደ አንድ መንግሥት በመቋቋም በሦስቱ ታላላቅ ነገሥታት፡- በሳኦል፣
በዳዊትና በሰሎሞን ሲመሩ የቆዩበት ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ዋና ተዋናይ የሆነው ዳዊት እግዚአብሔር እንደልቤ ያለው፣ በአምላኩ
የታመነ፣ በርካታ ጠላቶችን ድል ያደረገ እስራኤላውያን የሚመኩበት ታላቅ ንጉሥ ነበረ። ይህ ዘመን ዳዊት መዝሙራቱን፣ ሰሎሞንም የጥበብ
መጻሕፍቱን የጻፉበት ጊዜ ሲሆን በአንጻራዊነት ሲታይ የእስራኤላውያን መልካም የእረፍት ዘመን ነበረ ማለት ይቻላል።
፩ኛ ዜና መዋዕል - ፪ኛ ዜና መዋዕል
ሩብ ድረስ ከላይ ያለውን ከዳዊት - ሰሎሞን ያለውን ታሪክ የሚደግም ነው። አንዳንድ መምህራን እንደሚሉት ከላይ በመጽሐፈ ነገሥት በአብዛኛው የሚናገረው
የቤተ-ክህነቱን ጉዳይ ሲሆን በዚህ በዜና መዋዕል ደግሞ የቤተ-መንግሥቱን ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ይሰጠዋል።
በ፩ኛ ነገሥት አጋማሽ፣ በ፪ኛ ነገሥት
እና በቀሪው ፪ኛ ዜና መዋዕል - በዚህ ክፍል በ፲፪ቱ ነገዶች የተዋቀረው ጠንካራው የእስራኤል መንግሥት በሰሎሞን ልጆች ለሁለት
እንደተከፈለ ይገልጻል። በዚህም ፲ሩ ነገድ በሰሜን እስራኤል ተብሎ የተጠራው በኋላ በአሦራውያን ተማረክ፣ ሁለቱ ነገድ በደቡብ ይሁዳ
ተብሎ የተጠራ ሲሆን ከሰሜኑ የእስራኤል ምርኮ በኋላ በባቢሎናውያን ተማረከ።
ስለይሁዳና ስለእስራኤል ነገሥታት፣
ስለነቢያትና ስለሌሎችም ለመረዳት ከዚህ በታች የተመለከተውን ሰንጠረዥ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የተወሰደውን ብንመለከት ታሪኩን
ይበልጥ ግለጽ ያደርገዋል።
በመጽሐፈ ዕዝራ፣ ነህምያና አስቴር፡-
የምርኮ ዘመን ቆይታና ከምርኮ መልስ በኋላ ያለውን የእስራኤላውያንን ታሪክ ይናገራል። ብዙዎቹ እስራኤላውያን ከምርኮ በኋላ ወደ
ሃገራቸው አልተመለሱም፤ በያሉበት ሃገር ምኩራብ በመሥራት አምልኮአቸውን ለመቀጠል ሞክረዋል። ቀደም ሲል የተማረኩት አይሁድ በኋላ
በነገሠው በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ፈቃድ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።
እስራኤላውያን ከምርኮ ወደ ሃገራቸው
ከተመለሱ በኋለ ምንም እንኳ እንደቀድሞው ራሱን የቻለ መንግሥት አቋቁመው ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው እንደ ሃገር ነጻ ሆነው ለመኖር
ባይበቁም በወቅቱ በነበረው የፋርስ ቅኝ አገዛዝ እንደ አንድ ጠቅላይ ግዛት ሆነው ቤተ መቅደሱን ሰርተው አምልኳቸውንና ኑሮአቸውን
ቀጥለዋል። ይህ የእስራኤል ወደ ሃገራቸው መመለስ የተፈጸመው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ400 ዓመተ ዓለም ነው።
ከዚህ በኋላ እስከ ክርስቶስ ልደት
ያለው 400 ዓመት የጸጥታ ዘመን ይባላል። ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን እንደተከናወነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈ ነገር
ስለሌለ ነው። ስለሆነም ይህ የብሉይ ኪዳን ታሪክ መጨረሻ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ በኋላ የሚገኙት የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ማለትም
የቅኔና የመዝሙራት እንዲሁም የነቢያት መጻሕፍት ሌላ ቀጣይ ታሪክ ሳይሆኑ ከላይ ባየነው የእስራኤላውያን የታሪክ ክፍል ውስጥ በተለያየ
ጊዜ የተጻፉና የተነገሩ ናቸው።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ፫ኛውን
የብሉይ ኪዳን ይዘት የሆነውን የቅኔና የጥበብ ክፍልን እናያለን።
ይቆየን።
No comments:
Post a Comment
አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment