Wednesday, November 21, 2012

ብሉይ ኪዳን - የመዝሙርና የጥበብ ክፍል


በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን የሚገኙት መጻሕፍት በሥነጽሑፋዊ ይዘታቸው ከአራት እንደሚከፈሉ በገለጽነው መሠረት ካሁን ቀደም የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ማለትም የኦሪት እና የታሪክ ክፍል የሚሉትን በየተራ አይተናል። ፫ኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል የሆነው የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት ጠቅለል ያለ ዳሰሳ ለዛሬ እናያለን።

የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት የቅኔ፣ የግጥም መጻሕፍት በመባል የሚታወቁ ሲሆን እነዚህም በሦስት ጸሐፍያን- በኢዮብ፣ በዳዊትና በሰሎሞን የተጻፉት አምስት መጻሕፍት መጽሐፈ-ኢዮብ፣ መዝሙረ-ዳዊት፣ (የመዝሙር መጻሕፍት) መጽሐፈ-ምሳሌ፣ መጽሐፈ-መክብብ እና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን (የጥበብ መጻሕፍት) ናቸው። ኢዮብ በየትኛው ዘመን ይኖር እንደነበረ በግልጥ የተቀመጠ ነገር የለም። ብዙ መምህራን ኢዮብ በቀደምት አበው በነያዕቆብ እና በነኤሳው ዘመን የነበረ መሆኑን ይናገራሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት (ከ፷፮ቱ) መጽሐፈ ኢዮብ ቀደምት ሲሆን በ፹፩ዱ መጽሐፈ ሄኖክ የመጀመሪያው መሆኑ ይታወቃል። ዳዊትና ሰሎሞን ከሳኦል ቀጥሎ እስራኤልን የገዙ የመጀመሪያዎቹ ነገሥታት ሲሆኑ የቅኔና የመዝሙር መጻሕፍቶቻቸው እስራኤላውያን ምድረ-ርስት ከነዓንን ከወረሱ በኋላ በነበረው የተረጋጋ ዘመን ማለትም በመጽሐፈ-ሳሙኤል እና መጽሐፈ-ነገሥት ዘመን ታሪክ ውስጥ የተጻፉ ናቸው።

መዝሙር/ግጥም በቀላሉ እና በሚስብ መልኩ መልእክትን ለማስተላለፍ የሚያገለግል አንድ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ነው። እግዚአብሔር ቃሉንና መልእክቱን ለሰዎች ለማስተላለፍ ከተጠቀመበት ዘዴ አንዱ በግጥም መልክ ማድረጉ ነው። ከስድ ንባብ ይልቅ ግጥም ምን ያህል እንደሚቀል መልእክቱን በቀላሉ ለመረዳት እንደሚያስችል በተለይም ግጥሙ ሰምና ወርቅ ለበስ ቅኔያዊ ከሆነ በጥቂት ቃላት ብዙ ሃሳብ መግለጽ እነደሚቻል ሁላችን በአማርኛ ቋንቋችን እናውቀዋለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግጥም/በመዝሙር መልክ የተጻፉ መጻሕፍት እነዚህ የመዝሙርና የጥበብ የተባሉት አምስቱ መጻሕፍት ብቻ አይደሉም። በኦሪትና በታሪክ እንዲሁም በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ በተለያዩ ምዕራፎች ግጥም/መዝሙሮችን እናገኛለን። እንዲያውም የብሉይ ኪዳን አንድ ሦስተኛው መዝሙር/ግጥም እንደሆነ ይነገራል። እነዚህ የመዝሙር መጻሕፍት በመጀመሪያ በተጻፉባቸው ቋንቋዎች ግጥም ስለሆኑ ቤት ይመቱ ነበር። ወደ ሌላ ቋንቋ ሲተረጉሙ ግን ቤት መምታት እንዳልቻሉ መምህራን ይናገራሉ።

የመዝሙርና የቅኔ መጻሕፍትን ከሌሎች በስድ ንባብና በታሪክ መልክ ከተጻፉት መጻሕፍት በተለየ መልኩ ማንበብና መረዳት ይጠይቃል። መቼም አንድ ገጣሚ የሚጽፍልንን ግጥም በግጥም ደንብ ካላየነው ወይም በስድ ንባብ አካሄድ ብናነበው ውበቱንም፡ መልእክቱንም እናጠፋዋለን። ምናልባት ገጣሚውም ቢሰማን ቅር ይለዋል።  የሚከተለውን ግጥም እንመልከት።
አብ አልሰጠኝ ብየ ምነው መናደዴ፣
ለወልድ አልነግርም ወይ ለሥጋ ዘመዴ።

ይህ ግጥም አጻጻፉ ፡ በየስንኙ (በየመስመሩ) ቤት በመምታት- ቤት በመድፋት፤ አነባበቡ በተለየ ቅላጼ ና በማስረገጥ፣ መልእክቱም ቅኔያዊ ስለሆነ በሰምና ወርቅ መሠረት ልናነበው ልንረዳው ያስፈልጋል። ስለዚህ የግጥም/የመዝሙር መጻሕፍትን ማንበብ፣ መተርጎም፣ እና መረዳት ያለብን በግጥም ደንብ መሠረት ሊሆን ይገባል።  ይህን ግጥም ወደ ሌላ ቋንቋ እንተርጉመው ብንል ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን፡ ውበቱም እንደሚጠፋ፣ መልእክቱም በአግባቡ ሊተላለፍ እንደማይችል ግልጽ ነው። ከዚህም ጋር የግጥም አጻጻፍ ደንብ በየቋንቋው የተለያየ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። ይሁንና ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህን መጻሕፍት በምናነብበት ጊዜ በተቻለ መጠን በግጥም /በመዝሙር የሥነ-ጽሑፍ አግባብ መሠረት ልናነባቸውና ልንተረጉማቸው እንደሚገባ አስቀድመን ማወቅ አለብን።


ስለዚህ የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት በተለየ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት የተጻፉ ልዩ መልእክት ያላቸው መሆናቸውን እና የተለየ የንባብና አተረጓጎም ስልት እንደሚፈልጉ ልናስተውል ይገባናል። እነዚህ መዝሙራት/ግጥሞች ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የተለያየ ቅርጽና አደረጃጀት ሊኖራቸው ይችላል።
፩. ግጥሞቹ በየሁለት መስመር ወይም ከዚያ በላይ ተመሳሳይ አሳብ ሊይዙ፡ ሊደጋግሙ ይችላሉ።
ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፣
 ምድር ሁሉ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ
ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ
ክብሩን ለአሕዛብ
ተኣምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ     መዝ ፺፭፣፩-፫።
፪. በየሁለት መስመር ሲታይ ሁለተኛው መስመር የመጀመሪያውን አሳብ ተቃራኒ ጉዳይ ሊይዝ ይችላል። መጽሐፈ ምሳሌ በአብዛኛው የዚህ ዓይነት ጠባይ/አካሄድ አለው።
                 ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች
                 ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች
         በቅን የሚሄድ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል
         መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል።       ምሳ ፲፬፣፩-፪።
፫. በየሁለት ወይም ከዚያ በላይ መስመሮች ሲታይ የመጀመሪያው መስመር /ቃላት የሁለተኛው መስመር መደምደሚያ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። በሌላ አባባል የሃሳቡ ቅደም ተከተል ከታች ወደላይ - መጀመሪያ የታችኛውን ከዚያ የላይኛውን መስመር ስናነበው ሊሆን ይችላል።
         ምስጉን ነው፣ በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣
         በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣
         በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።    መዝ ፩፣፩።
፬. ግጥሞች መዝሙር እንደመሆናቸው መጠን የክፍሉን ዋና ሃሳብ የሚያመለክቱ የተለዩ ስንኞች ሲደጋገሙ ልናገኝ እናገኛለን። በአማርኛ መዝሙሮች አዝማች እንደምንለው ያለ ማለት ነው።
መዝ ፻፴፭ -  ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፡  (በየመስመሩ)
መዝ ፻፮ - በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥   ከመከራቸውም አዳናቸው፣    (፬ ጊዜ)
፭. አንዳንድ ግጥሞች በምሳሌያዊ መልክ የተነገሩ ስለሚሆኑ መልእክታቸውን በምሳሌያዊ አገላለጽ ይበልጥ ጉልህ ሆኖ ይገኛል።
ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥
አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። መዝ ፵፩፣፩
የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት በውስጣቸው ጸሎት፣ ምስጋና፣ ትምህርት፣ምክር… ይዘዋል። መዝሙሮቹ በአብዛኛው የጸሐፊውን ስሜት የሚገልጹ ግጥሞች ናቸው። ስሜት ሲባል ጸሐፊው ካጋጠመው ወይም ከደረሰበት ሁኔታ አንጻር መደሰቱን፣ ማዘኑን፣ በመግለጽ ወይም በፍቅር፣ በቁጣ፣ በአክብሮት፣… ስሜት ውስጥ ሆኖ የጻፋቸው/ የገጠማቸው ስለሚሆኑ በምናነብበት ጊዜ የጸሐፊውን ስሜት ልንጋራ ያስፈልጋል።
ኢዮብ ከደረሰበት ፈተና አንጻር የነበረበትን ምሬት፣ ወዳጆቹ በራሳቸው ጥበብና ሃሳብ ሊያጽናኑት ሲሞክሩ በኋላም በፈተናው ካጣው ሃብት በላይ እግዚአብሔር እንደባረከውና ለበጎ ያደረገለት መሆኑን በመጨረሻ በማስተዋሉ፣ … በእነዚህ ስሜቶች ሆኖ ጽፎአል።
ዳዊት ከሕይወቱ አንጻር በብዙ ፈተና እና ውጣ ውረድ እንዳለፈ ታሪኩ ይናገራል። ከዚህ አንጻር መዝሙሮች በተለያየ ስሜት ሆነው የተጻፉ በመሆናቸው በሃዘን ጊዜ፣ በደስታ ጊዜ፣ በጭንቀት ጊዜ…. ወዘተ.. እየተባሉ በመከፋፈል ሊነበቡ እንደሚችሉ በብዙ ጥናቶች ይታወቃል።
ሰሎሞን በዚች ምድር ላይ እንደርሱ ያለ ጠቢብ የለም የተባለለት በመሆኑ በዓለም ላይ አሉ የተባሉትን ዝና፣ ጥበብ እና ሃብት ቢጨብጥም ትርጉም ስላልሰጡት የዓለምን ከንቱነት የመሰከረ በተሰጠው ጥበብም በርካታ ቀጥተኛ ምክሮችን በምሳሌዎቹ ያስተላለፈ ታላቅ ሰው እንደሆነ ይታወቃል። እርሱ የጻፋቸው የጥበብ መጻሕፍት ይባላሉ።
እንግዲህ የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት እነዚህንና መሰል የሆኑ የተለዩ የሥነ ጽሑፍ ደንቦች፣ የጸሐፊዎች ስሜቶች ስላሉአቸው በዚያ መሠረት ልናነባቸው፣ ልንተረጉማቸው ይገባል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ የትንቢት ክፍልን አጠቃላይ ዳሰሳ እናያለን፤
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment