Wednesday, November 23, 2011

በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት



በታሪክም ሆነ በተሞክሮ እንደምናውቀው ሰው በክርስቶስ ላይ ባለው እምነቱ ይጸድቃል ይድናል እንጂ የሙሴን ሕግ በመፈጸሙ ወይም በራሱ ጥረትና ሥራ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
በክርስቶስ የተገኘው የመዳን እምነት ከኦሪት ሥራ እንጂ ከፍቅር ሥራ አልተለያየም። ስለዚህ ሐዋርያው፡-
«በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን አለመገረዝ አይጠቅምም::» አለ። ገላ 5;6
በክርስቶስ ከሆንን የክርስትናን ሃይማኖት ምሥጢር ለማስተዋል እንችላለን። ካልሆንን ግን ዓላማውን ስተናል። ከመንገድም ወጥተናል።
የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት በጥቅሉ ሲገለጥ፡
-አንደኛ ለቤዛነት - ሁለተኛ ለአርአያነት
ስለሆነ ሁለቱም በእኛ ላይ ተፈጻሚነት ሊኖራቸው የሚችለው:-
-የመጀመሪያውን በእምነት ስንቀበለው - ሁለተኛውን ክርስቶስን መስለን እንደ ክርስቶስ በመኖር በፍቅር ሥራ በተግባር ስንተረጉመው ነው። ሁለቱንም በአንድነት በመያዝ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥራው  በሕይወቱ፡ በትምህርቱና በተአምራቱ፡ በሕማሙና በሞቱ፡ በትንሣኤውና በዕርገቱ በዓለም ላይ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ያልታየና ያልተሰማ ተአምራዊ ታሪክ ሠርቶ የክርስትናን ሃይማኖት መሠረተ።
ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ እንደሆነ የሚያምኑትን ክርስቲያኖች ሁሉ ያጠቃልላል። የክርስትና እምነት ምንነት በክርስቶስ ማንነት ይተረጎማል።
« ብሉይ ኪዳን ቤተ አይሁድን በሞግዚትነት አሳድጎ ለወንጌል እንዳስረከበ አሕዛብንም ፍልስፍናቸው (ሕገ-ልቦና) ወደ ክርስቶስ እንዳደረሰ ይነገራል። (ብሉይ ኪዳን ወደ ክርስቶስ ያላደረሳቸው፡ ፍልስፍና ወደ ክህደት የመራቸውም እንዳሉ አይዘነጋም።)
እውነተኛው አምልኮተ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚችለው በራሱ በእግዚአብሔር በኩል ብቻ ነው።
ከጥንት ጀምሮ በመረጣቸው ወገኖች አማካይነት ለዓለም ሁሉ ያዘጋጀውን የማዳን ምሥጢር ቀስ በቀስ በጊዜው ገለጠላቸው። በመጀመሪያ በቤተ እስራኤል- ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያን፡ በፊተኛው በትንቢትና በታሪክና በምሳሌ በኋለኛው በአማናዊነትና በፍጹምነት ተገልጧል።
ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት
በሊቀ-ጉባዔ አባ አበራ በቀለ
መጽሐፍ የተወሰደ ከገጽ 12 – 23
አሳታሚ ማኅበረ-ቅዱሳን 1996 /

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment