Monday, May 21, 2012

የአማርኛ ትርጉሞች ንጽጽር

Amharic Translations, read in pdf here

መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ከተጻፈባቸው እናት ቋንቋዎች በኋላ በዓለም ላይ ወደ ብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በተመሳሳይ ቋንቋም ቢሆን ትርጉሙ በየጊዜው ይሻሻላል። ምክንያቱም በሥነ-ልሳን ትምህርት እንደሚታወቀው ቋንቋ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይሞታል። ለምሳሌ የራሳችን የአማርኛ ቋንቋን ብንወስድ ከዛሬ 200 ዓመት በፊት የነበረው አማርኛ እና የአሁኑ አማርኛ በአነጋገርም፡ በአጻጻፍም ብዙ ልዩነቶች አሉት። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት እስኪ ከማቴዎስ ወንጌል አንዱን ክፍል የተለያዩ የአማርኛ ትርጉሞችን እንይ።
የማቴዎስ ወንጌል ም ፯፣፩-፲፬  በልዩ ልዩ የአማርኛ ትርጉሞች፡
የቀድሞ ትርጉም የ1870ዎቹ፡
 አትፍረዱ፡ እንዳይፈረድባችሁ። በፈረዳችሁት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፡ በምትሰፍሩበትም መስፈርያ ይሰፈርባችኋልና።
ለምንስ በወንድምህ ዓይን ያለውን ሰንጣቂ ታያለህ። ዓይንህም ያለውን መሰሶ አትመለከትም። እንዴትስ ወንድምህን ትለዋለህ፡ተወኝ ካይንህ ሰንጣቂ ላውጣልህ። እነሆ መሰሶም ዓይንህ ነው። አንተ ግብዝ አስቀድመህ መሰሶ ካይንህ አውጣ። ከዘያ በኋላም ታያለህ፡ ሰንጣቂውን ከወንድምህ ዓይን ታውጣ ዘንድ።
የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፡ እንቆችሁንም አትጣሉ፡ በእርዮች ፊት፡ በግሮቻቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክስዋችሁ።
ለምኑ ይሰጣችኋልም። እሹ ታገኙማላችሁ። ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋልም። የለመነ ሁሉ ይወስዳልና። የፈለገም ያገኛል፡ ደጅም ለመታ ይከፈትለታል።
ወይስ ምን ሰው ከላንት ነው ልጁ እንጀራ ቢለምነው በውኑ ደንጊያ ይሰጠዋል። ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋል። 


እንኪያስ እላንት ክፉ ስትሆኑ ለልጆቻችሁም መልካም መስጠት ካወቃችሁ እንዴት እጅግ የሰማዩ አባታችሁ ለሚለምነው መልካም ነገር ይሰጠዋል።
ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እንዲሁ ደግሞ እላንትም አድርጉላቸው ኦሪትም፡ ነቢያትም ይህ ነውና።
በጨነቀችው ደጅ ግቡ። ደጁ የሰፋ ነውና መንገዱም የተዘረጋ ነው ወደ ጥፋት የሚወስድ፡ ወደርሱም የሚገቡ ብዙ ናቸው።  ደጅቱም የጨነቀች ናት መንገድም የፀበበች ወደ ሕይወት የምትመራ፡ ጥቂትም ናቸው የሚያገኙዋት።

በዚህ የቀድሞ ትርጉም እንደሚታየው አንዳንድ ቃላት ለአሁኑ ዘመን ትውልድ እንግዳ ናቸው። ለምሳሌ፡ እላንት (እናንተ)፡ በጨነቀችው (በጠበበችው) የሚሉትን ማየት ይቻላል። የሰዋሰው አወቃቀሩም ግሱ ሲቀድም እናገኘዋለን። ለምሳሌ ከዘያ በኋላም ታያለህ፡ ሰንጣቂውን ከወንድምህ ዓይን ታውጣ ዘንድ።…ጥቂትም ናቸው የሚያገኙዋት።
እንግዲህ እነዚህ የቋንቋ ጠባዮች መጽሐፍ ቅዱስን እንደገና ተሻሽሎ እንዲተረጎም እንዳደረጉት እንረዳለን።

የ1954 ዓ/ም የጃን ሆይ ትርጉም
እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።
በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን?
እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?
እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።
በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤
ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።

በዚህ ትርጉም እንደምናየው ከቀድሞው የተሻሻሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፡ እሹ..ፈልጉ፡ ደጅ ምቱ  ..መዝጊያን አንኳኩ። በጨነቀችው ደጅ… በጠበበችው ደጅ…. ተብለው ተቀይረዋል።

የ1980 ዓ/ም  81ዱ እትም
በሌሎች ላይ መፍረድ እንደማይገባ
እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ። በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈርያ ይሰፈርባችኋልና። በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ? በአንተ ዐይን ያለውን ምሰሶ ግን ለምን አታስተውልም? ወንድምህን በዐይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ ተወኝ እንዴት ትለዋለህ? እነሆም፥ በአንተ ዐይን ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ አስቀድመህ በአንተ ያለውን ምሰሶ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።
በእግራቸው እንዳይረግጡት፥ ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁአችሁንም በዕሪያዎች ፊት አታኑሩ።
ለምኑ ይሰጣችኋልም፤ ፈልጉ ታገኛላችሁም፤ ደጅ ምቱ፥ ይከፈትላችኋልም። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛልና፥ ደጅ ለሚመታም ይከፈትለታልና። ከእናንተ ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ሰው ማነው? ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን? እንግዲህ እናንተ ከፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካሙን ነገር እንዴት አብልጦ ይሰጣቸው ይሆን?
ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፥ነቢያትም የሚያዙት ይህ ነውና።
በጠባቢቱ በር
በጠባቢቱ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የምትወስድ ሰፊ በር፥ ሰፊ መንገድም አለችና፤ ወደ እርስዋም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የምትወስደው በር እጅግ ጠባብ፥ መንገድዋም ቀጭን ናትና፤ የሚገቡባትም ጥቂቶች ናቸው።

በዚህ ትርጉም እንደምናየው ለየክፍሉ ርእስ ተሰጥቷል። መዝያጊያን አንኳኩ…ደጅ ምቱ ተብሎ ወደ ቀድሞ ትርጉም ተመልሷል። ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና…ኦሪትም፥ነቢያትም የሚያዙት ይህ ነውና። ተብሎ ተሻሽሏል….
እንግዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ልዩ ትርጉሞች የተለያየ ቅርጽና ይዘት እንደሚኖር እናያለን። በአንድ ቋንቋ የተለያዩ ትርጉሞች ምን ያህል ልዩነት/መሻሻል እንደሚኖር ከላይ በአማርኛው የሦስት ትርጉሞችን ካየን በዚህ ዓይነት ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ለሚደረግ ትርጉም በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ልዩነት እንዲያውም የባሰ/በጣም የተሻሻለ ጉዳይ ሊገጥመን ይችላል ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ወደ ፊት ቀስ በቀስ እያየን እንሄዳለን።
በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ልዩ ትርጉሞች ማወቅ እና እያዛመዱ ማጥናት  በጣም አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ እናስተውላለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment