Saturday, December 10, 2011

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት


መጽሐፍ ቅዱስ ፈቃደኛ በሆነ ልብ ለሚያዳምጡት ሰዎች የእግዚአብሔር ድምጽ የሚሰማበት መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔር ድምጽ ደግሞ በኃጢአት የወደቀውን ለማንሣት፡ የጎሰቆለውንና ያደፈውን ለማደስና ለማንጻት፡ የደከመውን ለማበርታት ሙሉ ኃይል አለው።መጽሐፍ ቅዱስ መጻፉም ለዚሁ ዓላማ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀምና እግዚአብሔር ከሰው ልጅ የሚፈልገውን ሁሉ ለመፈጸም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ፡ የአካሔድ ባህልና አጠቃላይ ታሪክ መረዳት፡ ማጥናትና ማገናዘብ ይገባል። ቅዱሳን አበው በሕይወታቸው እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለማስደሰት የቻሉት እግዚአብሔር በመጽሐፍ የተናገራቸውን በማስተዋላቸውና በሥራ በመግለጣቸው ነው።
ባለንበት ዘመንም ምእመናን እግዚአብሔርን እንደ አምላክነቱ ለማወቅና ለማመን፡ ቅዱሳን አበውን ለመከተልና እነርሱን ለመምሰል እንዲሁም እነርሱ ያገኙትን አምላካዊ ስጦታ ለማግኘት አበው የያዙትን፡ የተመሩበትንና የተጠቀሙበትን መጽሐፍ ቅዱስ ልናውቀው፡ ልንረዳውና ልንጠቀምበት ይገባል።
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ የተገለጠበት መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔርን አሳብ ደግሞ በሥጋዊ በደማዊ አእምሮ መረዳት አይቻልም። በመሆኑም ጥልቅና ምጡቅ የሆነው የእግዚአብሔር አሳብ የተገለጠበትን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቦ ለመረዳት ከአንባቢያን አፍኣዊና ውስጣዊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቃል። 


መጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የሆኑ ባሕሎች አሉት። በውስጡ የሚገኙ አያሌ አባባሎችም አሉ። እነዚህን ባህሎችና አባባሎች ሳይረዳ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ሰው የመጽሐፉን ጭብጥ ሊገነዘብና ሕይወት ሊያገኝበት አይችልም። የተረዳ ቢመስለውም ከሚኖርበት ኅብረተሰብ ባህልና አባባል አንጻር ብቻ ስለሚመለከተውና ስለሚገነዘበው ለከባድ ስህተት ይዳረጋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው የእግዚአብሔር ሥራ በቦታ፡ በጊዜና በተለያዩ መንገዶች የተከናወነ ነው።እነዚህን የእግዚአብሔርን ሥራዎች ያስተናገዱ ቦታዎችን ማወቅ ለመንፈሳዊ ሕይወት ዕውቀት ማደግ የራሱ ድርሻ አለው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት-፪ --- መግቢያ
በሊቀ-ጠበብት ሐረገወይን አገዘ እና ቀሲስ ስንታየሁ አባተ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ-ቅዱሳን
ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተዘጋጀ።
የካቲት ፳፻፫ ዓ.ም -------  የተወሰደ
ባለፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያዎች እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ለመረዳት ጠቅለል ባለ መልኩ በሁለት አቅጣቻ የምናያቸው ጉዳዮች አሉ።
፩- ከኛ የሚያስፈልጉ ቅድመ-ዝግጅቶች፡---ማመን፡ መጸለይና መታዘዝ
፪- ስለራሱ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ የሚገቡን መረጃዎች፡- ሃገሮች፡ ሕዝቦች፡ ከተሞች፡ ባሕሎች፡አባባሎች፡መልክዓ-ምድር፡ ተራሮች፡ወንዞች፡ገንዘቦች ካርታዎች፡መለኪያዎች፡ንጽጽሮች፡ጥሬቃሎች፡ ወዘተ… ናቸው።
በዚህ የትምህርት ክፍል እነዚህን በየተራ ከምሳሌ ጋር እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀጣይ ጊዜ በቅድሚያ ማመን ስለሚገባን ስለእግዚአብሔር (ምሥጢረ-ሥላሴ) በአጭሩ እናያለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment