Monday, June 4, 2012

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢትና የዓለም ፍጻሜ-ክፍል ፩


የዓለም ፍጻሜ መቼና እንዴት ነው? ይህ ሁሉንም ሰዎች የሚያስጨንቅ ጉዳይ ነው። ለክርስቲያን ይህ ጥያቄ አሳሳቢ አይደለም። ሁልጊዜ ተዘጋጅቶ መጠበቅ እንዳለበት ያውቃልና። ይሁን እንጂ ከዛሬ ፪ሺ ዓመት በፊት ሐዋርያት ጌታን ይህንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቀውት የመለሰላቸውን ትንቢታዊ መልስ ዛሬ እንዴት እየተፈጸመ እንዳለ ከመረጃ ጋር በዚህ ጽሑፍ እናያለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በዘመኑ እንዴት እየተፈጸሙ እንዳሉ ማስተዋል አንዱ ርእሰ-ጉዳይ ነውና፡፡ ለዛሬ ለመጀመሪያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ የተናገረውን ትንቢታዊ ቃል አፈጻጸም እንመልከት።
/መረጃው ከተለያዩ ምንጮች የተገኘ መሆኑን እና የቀን አቆጣጠሩ የአውሮፓውያን መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።/
ማቴ ፳፬፡፫ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።»
ቁ.፭፡ «ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።»
በታሪክ እንደተዘገበው እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ ቦታዎች ከ12ሺ የማያንሱ ሰዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ፡ /እግዚአብሔር ነኝ፡ ወይም መንፈስ ቅዱስ ነኝ በማለት በተለያየ ጊዜ ተነስተዋል።  ለአብነት ያህል ጆን ኒኮላስ ቶም በእንግሊዝ ሃገር በ1834 ፣ ሚራንዳ በአሜሪካ ግዛት በፍሎሪዳ- ሚያሚ ከተማ በ1976፣  ዊሊያም ዴቪስ በ1881 በዋሽንግተን፣  ባሃኡላ በ1844 በስሎቫኪያ…. የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህና ሌሎችም በወቅቱ ብዙ ተከታዮች ያገኙ ነበሩ። ይሁንና ሁሉም አንድ ባንድ አልፈዋል። አንዳንዶቹም ሃይማኖቶችን መስርተው ተከታዮቻቸው እስከዛሬ አሉ።
ቁ. ፮፡ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤»
ዓለማችን ጦርነትን ያሳለፈችባቸው በርካታ ዓመታት እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል። እንደ 20ኛው ክፍለ ዘመን ግን በጦርነት የታመሰችበት ጊዜ የለም።


 በየዜና ማሰራጫው ከምንሰማቸው አብዛኞቹ የጦርነት ወሬዎች ናቸው። በታሪክም ስንመለከት 1ኛው የዓለም ጦርነት በተካሄደ 40 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተካሂዷል። ይህ ማለት 1ኛውን የዓለም ጦርነት ያካሄደው ያው ትውልድ ሁለተኛውን የዓለምን ጦርነት ደግሞ አድርጎታል ማለት ነው። ከ1914-1918 እና 1939-1945።
በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት - ከ20 ሚሊየን በላይ ሰው የሞተ ሲሆን በታሪክ አስከፊ በተባለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ60 ሚሊየን ሕዝብ በላይ አልቋል። ይህም ቁጥር በወቅቱ የዓለምን ሕዝብ 2.5% ነበረ፤
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም ሰላም ይሰፍንባታል ተብሎ ቢገመትም በተለያዩ ግጭቶች ከዚያ ወዲህ እንኳ 23 ሚሊየን በላይ ሰው ሞቷል። ሰላም ይሆናል ቢባልም እንኳን ሰላም ሊሆን በየቦታው ጦርነቶች የተስፋፉ ሲሆን የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂውም እየተሻሻለ፣ የጦር መሣሪያ እሽቅድድሙ እየጨመረ ዓለማችን ወደ ባሰ የጦርነት ስጋት እንድትገባ አድርጓታል።
በ1993 ዓ/ም ብቻ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች 29 ጦርነቶች እንደተደረጉ ተመዝግቧል። የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል መረጃዎች እንደሚያሳዩት፡ እኤአ ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ በጦርነት ብቻ መቶ ሚሊየን ዜጎች ሕይወታቸው አልፎአል። ሌላ መረጃ እንደሚያሳየውም በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተደረጉ ጦርነቶች 160 ሚሊየን ሰው አልቋል።
በየቦታው ግጭት፡ጦርነት፡ እልቂት መስማት ለዚህ ዘመን ትውልድ ተራ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ጌታ እንደተናገረው  ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
ቁ ፯፡ «ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥»
ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳል ባለው ቃል በዘመናችን ስናየው በአንድ ሃገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሕዝቦች/ጎሳዎች እርስ በርስ ያደረጉትን ግጭቶች እናስታውሳለን። በታሪክ እንደተዘገበው ከሌሎች ሃገሮች በበለጠ በቻይና ከ755 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት 6 የእርስ በርስ ጦርነቶች ተካሂደዋል። በዚህም ከ200 ሚሊየን በላይ ሕዝብ አልቋል። ሌሎችን የቅርብ ጊዜያት የእርስ በርስ ጦርነቶች የሚከተሉት ጥቂቶች ናቸው።
ተ.ቁ
ጦርነት የተካሄደበት ሃገር
ዓመተ ምህረት
የቆየበት ዓመት
ሟች ሰው
1
የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት
1861 – 1865
5 ዓመት
600 ሺ  በላይ
2
በሶቪየት ህብረት- አብዮት
1917 - 1953
37 ዓመት
30 ሚሊየን በላይ
3
ሩዋንዳ - የጎሳ ግጭት
1994
1 ዓመት
700 ሺ በላይ
4
ሱዳን-ዳርፉር ግጭት
2003-2010
8 ዓመት
300 ሺ በላይ
5
አፍጋኒስታን
1979 - አሁን
32 ዓመት
3 ሚሊየን በላይ

መንግሥት በመንግሥት ላይ ባለው አንዱ ሃገር ከሌላው ሃገር የተደረጉ ብዙ ጦርነቶች ነበሩ። ከእነዚህም  የሚከተሉትን ጥቂቶችን ማስታወስ ይቻላል።
ተ.ቁ
ጦርነት ያካሄዱ ሃገሮች
ዓመተ ምህረት
የቆየበት ዓመት
ሟች ሰው
1
የመስቀል ጦርነት/ እስራኤል ቅድስት ሃገር
1095-1291
196 ዓመት/በተለያዩ ጊዜያት
2 ሚሊየን በላይ
2
ሞንጎሊያ ና አካባቢው
1207 -1472
200 ዓመት በላይ
40 ሚሊየን በላይ
3
ሚክሲኮና አሜሪካ
1911-1920
10 ዓመት
1.5 ሚሊየን በላይ
4
ኮርያ ና አካባቢው
1950-1953
4 ዓመት
3 ሚሊየን በላይ
5
ኢራቅና ኢራን
1980- 1988
9 ዓመት
1.5 ሚሊየን
በጎረቤት ሃገሮች በየጊዜው የሚካሄዱ ጦርነቶች በርካታ ናቸው። ዓመታቱ እየተቆጠሩ ሲመጡ ጦርነቶችም እየጨመሩ፡ ሁኔታቸውም እየከፋ እንደመጣ በታሪክ እየታየ ያለ እውነታ ነው። ከዚህ እንደምናየው የጌታ ቃል በአሁኑ ሰዓት በእውን እየተፈጸመ ያለ አማናዊ ቃል መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን።
ብዙ ሃገራት ለመከላከያ የሚመድበቱ በጀት ከፍተኛ ነው። በዓለማችን ለጦርነት የሚወጣው ወጭ ከየትኛውም ሌሎች ወጭዎች በእጅጉ ይበልጣል። የጌታ ቃል እንዴት እየተፈጸመ እነደሆነና እኛም ወዴት እየሄድን እንደሆነ እንድናስብ እስኪ የሚከተለውን መረጃ እንይ።
ይቅርታ (በዲ/ን አሸናፊ መኮንን) ከሚለው መጽሐፍ  እንዳነበብኩት፡-
አሜሪካ ከኢራቅ ጋር ላደረገችው ጦርነት በመጀመሪያ ጊዜ 60 ቢሊየን ዶላር ስትመድብ የዓለምን ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠፈ ያለውን ኤድስን ለመከላከል ግን የመደበችው 500 ሚሊየን ዶላር ነበር።
ሕይወትን ለማዳን ከመደቡት ገንዘብ፡ ሕይወትን ለማጥፋት በብዙ ቢሊየን እጥፍ የመደቡት ሰዎች በክርስቲያንነታቸው የሚኮሩና ገንዘባቸው ላይ እንኳ ሳይቀር «በእግዚአብሔር እንታመናለን።» ብለው የጻፉ መሆናቸውን ስናስብ ይገርማል። …..
መንግሥታት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡት ለመድኃኒት መርጫ አውሮፕላኖች ሳይሆን ለቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ነው።… እያንዳንዱ ሃገር ለአንድ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን የሚያወጣውን ገንዘብ ቢሰጥ የምድሪቱን ድሆች መታደግ ይቻላል።…. ከአንድ የጦር አውሮፕላን የሚጣል አንድ ቦምብ ለገጠር መንደሮች አንድ መለስተኛ ክሊኒክ ይከፍታል።… የዓለምን ችግረኛ ሕጻናት ለመታደግ የበለጸጉት አገሮች የሃያ አራት ሰዓት የወታደራዊ ወጪያቸውን ቢሰጡ በቂ ነው።……..
በዚህ በምናየው እውነታም ሌላው የጌታ ቃል እየተፈጸመ እናገኛለን። ረሃብ እየተስፋፋ….
ማቴ ፳፬፣፯… ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ቀጣይ ክፍሎችን ከመረጃዎች ጋር እናያለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment