Melkam endehone aye, sebket, READ IN PDF
በመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ (ዘፍ ፩) እግዚአብሔር ፍጥረታትን በየቀኑ እየፈጠረ በመጨረሻ የሚናገረው ቃል «መልካም እንደሆነ አየ።» የሚል ነው። ይህም ሰባት ጊዜ ተጽፎአል። (ቁጥር ፬፡፲፩፡፲፫፡፲፱፡፳፪፡፳፭፡፴፩)።
ከርሱ በላይ ጥበበኛ የሌለ፡ ለሰዎች ጥበብን የሚሰጥ አምላክ የሠራውን ነገር ሁሉ መልካምነት የሚያረጋግጥለት ሌላ አካል ስለማይኖር ራሱ በዚህ ድንቅ ቃል እያረጋገጠ ፍጥረታትን ፈጥሯል። ሰዎች የሚሠሩትን ነገር ሰዎች ያጸድቃሉ፡ ይተቻሉ፡ ያሻሽላሉ ወይም ውድቅ ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ግን በሥራው ፍጹም ስለሆነ አንዳች እንከን ሊኖርበት ከቶ አይችልም። ሰዎች ሆነን ስንፈጠር ምንም እንኳ አዋቂነት ቢኖረንም ባለን የመረዳት አቅም ውስንነት ምክንያት ሁሉንም የርሱን ሥራዎች ለማየትም ሆነ ለመተቸት አንችልም።
አንድ የሚነገር ታሪክ አለ። ሰውየው ፈላስፋ ቢጤ ነውና በሚያያቸው ነገሮች ሁሉ አስተያየት መስጠት ይወዳል። ታዲያ አንድ ቀን መንገድ ሲሄድ ደከመውና በአንድ ሾላ ዛፍ ስር አረፍ አለ። ቀና ብሎ ሲመለከት ሾላው ዛፉ ትልቅ ነው፡ ፍሬው ግን ትንሽ ነው። አጠገቡ ደግሞ የዱባ ተክል ነበረና ሲመለከተው ዱባው ግንዱ ትንሽ ነው፡ ፍሬው ግን ትልቅ ነው መሬት ለመሬት ይጎተታል። ታዲያ ሰውየው ሁለቱን አነጻጸረና አንዲህ ሲል ተናገረ፡-
« እግዚአብሔር አነዚህን ሁለት ዕጽዋት የፈጠረ ቀን ተሳስቷል። ለትልቁ የሾላ ዛፍ ትንሽ ፍሬ፡ ለትንሹ የዱባ ተክል ትልቅ ፍሬ በመስጠት አዘዋውሮታል። ከዚያ ይልቅ ለትልቁ ትልቅ ፍሬ፡ ለትንሹ ትንሽ ፍሬ ሰጥቶ በየመጠናቸው ቢያደርጋቸው መልካም ነበረ።» አለ።
ይህን እያሰላሰለ ደክሞት ነበረና መሬት ላይ ጋደም ብሎ እንቅልፍ ያሸልበዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሆነ ነገር አፍንጫውን ይመታውና ይነቃል። ሲያይ አፍንጫው ደምቷል። ከዚያ ከደረቱ ላይ የሾላውን ፍሬ ያገኛል። ነፋስ የጣላት የሾላ ፍሬ አድምታዋለች። የርሱን አባባል አስታወሰ። እኔ ያልኩት ቢፈጸምና ያ ዱባ ከላይ ወድቆ ቢመታኝ…? …ወዲያው እንደተሳሳተ ተረዳና-- እግዚአብሔር ሆይ ያንተ ሥራ ትክክል ነው። እኔ ተሳስቻለሁ፡ ብሎ መሸነፉን አውቆ ንስሐ ገባ። አዎ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉም አንዳች እንከን የሌለበት መልካም ነው።
በእግዚአብሔር ሥራና አሠራር ላይ ምንም ማለት የማንችል ደካሞች መሆናችንን ልንረዳ ያስፈልጋል። ሥራውን ከማድነቅ እና እርሱን ከማመስገን በቀር አስተያየት ልንሰጥ አንችልም። ፍጥረታት የተፈጠሩት ለአንክሮ ለተዘክሮ ነውና። እግዚአብሔርን ለማድነቅ፡ እርሱንም ለማስታወስ።
« ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ። የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።» መዝ ፲፰፡፩
- መልካም እንደሆነ አየ። መልካም። ቃሉ የበጎ ነገር ማረጋገጫ ነው። ይህ የተነገረው የእግዚአብሔር ሥራ ምንጊዜም ቢሆን መልካም እንደሆነ እንዳንዘነጋ ነው። ያንጊዜ፡ አሁንም፡ ለወደፊትም እስከዘላለም እርሱ እግዚአብሔር ሥራውም ሁሉ መልካም ነው። ከዚህም ሌላ እኛ ውሎአችንን እንድንገመግም በተግባር እያስተማረን ነው። ልብ አድርጉ መልካም እንደ ሆነ አየ የሚለውን ቃል የተናገረው በየዕለቱ መጨረሻ (ማታ) ላይ ነው። እኛም ውሎአችንን በየዕለቱ ማታ ማታ መገምገም አለብን። መልካም ሥራ ነበረኝ ወይ? ብለን ራሳችንን እንድናይና ለቀጣዩ ዕለት በማስተካከያ እንድንጓዝ ነው። ዕለታዊ ሥራችን ሁልጊዜ መልካም ሊሆን ይገባል። «ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።» ገላ ፮፡፱።
-መልካም እንደሆነ አየ። አየ። መልካምነቱን ያረጋገጠው በማየት ነው። የአንድን ነገር መልካምነት የምናረጋግጠው በመስማት ሳይሆን በማየት ነው። በምንሰማቸው ነገሮች ብቻ ተመርተን ስለአንድ ነገር መልካምነት ወይም ክፉነት ማረጋገጥ እና ማውራት አንችልም። ሰዎች ስለአንድ ጉዳይ ሲሰሙና ሲያወሩ ቶሎ የሚቀናቸው ክፉነቱ እንጂ መልካምነቱ አይደለም። በፍጥነት የሚዛመተው መልካም ሳይሆን ክፉ ወሬ ነው። በዓለም ላይ በየዜና ማሠራጫውም ከሚወሩት ወሬዎች ክፉዎች ይበዛሉ። ነገሮችን በመልካም ጎን ማየት እንዴት መልካም ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ይለናል፡- « ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት (በሚያወሩበት) ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።» ፩ ጴጥ ፪፡ ፲፪።
በዘፍጥረት ምዕራፍ ፩ መጨረሻ፡- እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።ይላል ዘፍ ፡፴፩ ። ይህ የተነገረው በስድስተኛው ቀን ሰው ከተፈጠረ በኋላ ነው። የሰው መፈጠር እጅግ መልካም እንደሆነ እግዚአብሔር ተናገረ። እጅግ የሚለው ቃል ብልጫነትን ያሳያል። ሰው መልካም ብቻ ሳይሆን እጅግ መልካም ነው። በአፈጣጠሩ ሰውን ክፉ ነው ማለት እግዚአብሔርን መቃወም ነው። በአኗኗር ግን ሰው ክፉ መሥራት ጀመረ። «እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።» ዘፍ ፮፡፭። የሰው የክፋት ሥራ ምንጩ / መነሻው ግን ጥንተ-ጠላት ዲያብሎስ ነው። መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ። ዘፍ ፪፡፲፯። ከፍሬውም ወሰደችና በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።ዘፍ ፫፡፮። መልካም ብቻ ያውቁና ይኖሩ የነበሩት ክፉንም አወቁ።
በዚህ ምድር አሁን የምናያቸው የክፉ ሥራ ውጤቶች ከሰይጣን ናቸው። ስለዚህ ክፉን የሚያሠራውን ሰይጣንን እንጂ ሰዎችን ልንጠላ አይገባም። ውጊያችንም ከሥጋና ከደም ጋር (ከሰዎች ጋር) ሳይሆን ከሚጋልባቸው ከክፋት መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር፡ በጩኀትና በጉልበት ሳይሆን በጸሎትና በስግደት ሊሆን ይገባል። «መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።» ኤፌ ፮፡፲።
ምንም እንኳ በእግዚአብሔር እጅግ መልካም ሆነን ተፈጥረን የነበርን ሰዎች በፈቃዳችን በወሰድነው ምርጫ በዲያብሎስ ክፉ ሆነን ብንገኝም እግዚአብሔር ግን የኛን ክፉ ማንነት ለውጦ አዲስ ሰው (የቀድሞው እጅግ መልካም ሰው) ለማድረግ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮ እንዲሞትልን አድርጎአል። መልካም ሰዎች ሆነን መልካም ብቻ እንድንሠራ። እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌ ፪፡፲።
መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔር ዛሬም ሥራችን መልካም እንደሆነ ያያል። እግዚአብሔር እንደሚያየን ሆነን እንሥራ።
መልካም ሥራ:: መልካም ሥራ ብቻ::
|
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ዕብ ፲፫፡፳፩
ትክክል ነው አንድን ነገር እንዲህ ነው አንዲያ ነው ከማለት በፊት
ReplyDeleteትክክለኛነቱን በአይናችን በማየት ማረጋገጥ አለብን በወሬ በሰማነውም
ነገር እርግጠኛ ሆነን መናገር የለብንም ስለዚህ የአንድን ነገር መልካምነት
የምናውቀው እኛ እራሳችን በማየት ስናረጋግጥ ብቻ ነው፡፡
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው
ReplyDeleteGod is uniqe(work)
ReplyDeleteGod is always perfect
ReplyDeleteyou send TRUE messages that everybody should read it and live in
ReplyDelete