Tuesday, July 24, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዳሰሳ-ብሉይ ኪዳን



መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የዓለምና የሰው ዘሮችን ታሪክ ለመተረክ የተጻፈ / የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ በታሪክ ውስጥ በዘመናት እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች በቅደም ተከተል  እናገኝበታለን። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው አከፋፈሉ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብሎ የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዳቸው ወጥ የሆኑ የራሳቸው ታሪካዊ አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ ለአጠቃላይ ግንዛቤና ስለምን እንደሚያወሩ ለመረዳት በውስጣቸው ያለውን ታሪካዊ ይዘት ፍሰት በጥቅል መመልከቱ አስፈላጊ ነው።  በዚህም መሠረት ለዛሬ የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ዳሰሳ እናያለን።
ብሉይ ኪዳን ከዓለም መፈጠር እስከ ክርስቶስ ልደት ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። በዚህም ክፍል የኦሪት፣የታሪክ፣ የመዝሙራትና የነቢያት መጻሕፍት ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ በሆነው መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ ፲፩ ምዕራፎች መላውን ዓለም የሚወክል የነገሮችን ጅማሬ ያሳየናል። የዓለምን አፈጣጠር፣ የኃጢአት መጀመር፣ የቋንቋ መብዛት፣ የሰው ዘር መባዛት፣ ወዘተ… ይናገራል። ከምዕራፍ ፲፪ በኋላ ግን የአንድን ወገን ማለትም የእስራኤላውያንን ታሪክ ብቻ ይዞ ይሄዳል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው የዘመን ስፍር ፭ሺ ፭፻ መሠረት ከዘፍጥረት ፩ - ፲፩ (ከአዳም - አብርሃም) ያለው ክፍል የ፫ሺ ፭፻ ዓመት ታሪክ ሲሆን የቀረው ከዘፍጥረት ፲፪ - ክርስቶስ ልደት (ከአብርሃም - ክርስቶስ) ያለው የ፪ሺ ዓመት ታሪክ እንደሆነ ይነገራል። ብሉይ ኪዳን የተፈጸመው በ፭ሺ ፭፻ ዘመን ውስጥ ቢሆንም የተጻፈው ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ፩ሺ ፬፻ ዓመት  እስከ ፬፻ ዓመት- በ፩ሺ ዓመት ውስጥ ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ከሰዎች ጋር በውል /ኪዳን/ ለመሥራት ለሚያዘጋጀው ለመጀመሪያው ቃል ኪዳን (ለብሉይ ኪዳን) አንድን ሕዝብ እስራኤላውያንን በመምረጥ ለዚህም አብርሃምን በመጥራት ይጀምርና  ከዚያ በኋላ መላው ብሉይ ኪዳን እነዚህ የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት አንጻር የደረሰባቸውንና ያደረሱትን ጉዳዮች፣ (ታሪካቸውን) ይናገራል።
የመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን ክፍል አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀደምት እስራኤላውያን  አበው፡- አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አማካይነት እስራኤል የተባለ ሕዝብ ለራሱ እንዴት እንደመረጠ፣ ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ በመሴ እንዴት እንዳወጣቸውና በጉዞአቸው ሕግና ሥርዓቶችን በመስጠት እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ በማዘዝ ቃል የገባላቸውን ምድረ-ርስት ለማውረስ እንዴት እንዳዘጋጃቸው ይናገራል።




በታሪክ ክፍል ከሙሴ ቀጥሎ በተነሳው መሪያቸው በኢያሱ አማካይነት ቃል የገባላቸውን ምድረ-ርስት ካወረሳቸው በኋላ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥት ሆነው በንጉሥ እንዲተዳደሩ በጠየቁት መሠረት መጀመሪያ ሳኦልን በኋላም ዳዊትን የሰጣቸው ሲሆን ቀጥሎም በሰሎሞን ጊዜ ሰሜንና ደቡብ (እስራኤልና ይሁዳ) ተብለው ከሁሉት በመከፈላቸው ሁለቱም በየተራ በጠላት እንዴት እንደተማረኩና ወደ ዓለም እንደተበተኑ ይነግረናል።
የቅኔና የመዝሙራት መጻሐፍቱ በአብዛኛው በደህናው ጊዜ ማለትም በመንግሥት እየተዳደሩ በነበሩበት ወቅት በዳዊትና በሰሎሞን የተዘጋጁ የምስጋና፣ የጸሎት፣ የምክር መጻሕፍት ሲሆኑ የትንቢት መጻሕፍቱ ደግሞ ከመማረካቸው በፊት እና ከተማረኩ በኋላ እንደ ምክር፣ ተግሣጽ፣ ማስጠንቀቂያና ተስፋ ሆነው የተጻፉ ናቸው። በነቢያት የተነገሩት ትንቢቶች የተግባራዊነት ዳራ ግን በዚያ ወቅት ለእስራኤል ብቻ ተወስነው የሚቀሩ ሳይሆን በቀጣይ እግዚአብሔር ለመላው ዓለም በሚያዘጋጀው የወደፊት አዲስ ኪዳን ተፈጻሚነትን የሚያገኙ እንደ ሕጻኑ (ወልድ-ክርስቶስ) መወለድ ያሉ በርካታ መልእክቶችን ያዘሉ የንግርት ቃሎች ናቸው።
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን የመጻሕፍቱ ቅደም ተከተል መሠረት የሚናገርላቸውን ሕዝቦች የእስራኤላውያንን ሁኔታ ስንመለከት የተሰጣቸው ቃል-ኪዳን /ውል/ እስከሆነ ድረስ መላው ታሪኩ ከዚህ ኪዳን አንጻር የተያያዙ ክስተቶች ዳሰሳ እንደሚከተለው በሦስት ክፍሎች በሁለት አቅጣጫ ጠቅለል ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ።
ቃል ኪዳኑ (ብሉይ ኪዳኑን) መጀመር - ማክበር - ፍርድ ከሚለው ፍሰት አንጻር፡
፩. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር  ቃል ኪዳን እንዴት እንደጀመረ፡
ከኦሪት ዘፍጥረት - ኦሪት ዘዳግም ያለው ክፍል ይናገራል።
፪. ቀጥሎም እግዚአብሔር በአባቶቻቸው የገባላቸውን ምድረ-ርስት ከነዓንን የማውረስ ቃል-ኪዳን አንዴት እንዳከበረ፡  
ከመጽሐፈ-ኢያሱ ወልደ ነዌ -  ፪ኛ ሳሙኤል ያለው ክፍል ይናገራል።
፫. በመጨረሻ እስራኤላውያን የተገባላቸውንና የተፈጸመላቸውን ቃል-ኪዳን ሕጉን በመጠበቅ ባለማክበራቸው እንዴት በጦርነትና በምርኮ እንደተፈረደባቸው፡
                       ከ፩ኛ ነገሥት - ትንቢተ ሚልክያስ ያለው ክፍል ይናገራል።
ቃል ኪዳኑን (ብሉይ ኪዳኑን) ማክበር  - ፍርድ - ምሕረት በሚለው ፍሰት፡
፩. እግዚአብሔር በቀደምት አበው ቃል የገባላቸውን የከነዓንን ምድር የማውረስ ተስፋ እንዴት እንዳከበረ
            ከኦሪት ዘፍጥረት - መጽሐፈ መሳፍንት
፪. እስራኤላውያን ቃል ኪዳኑንና ሕጉን ባለመጠበቃቸው ወደ ጦርነትና ምርኮ እንዴት እንደተፈረደባቸው
            ከመጽሐፈ ሩት - መጽሐፈ ዜና መዋዕል
፫. እግዚአብሔር በምሕረቱ እንደገና እንዴት እንደሚሰበስባቸው  በነቢያት ተስፋ እንደሰጣቸው
            ከመጽሐፈ ዕዝራ - ትንቢተ ሚልክያስ ይናገራል።
የነቢያት መጻሕፍት በወቅቱ ለነበሩት ለእስራኤላውያን የፍርድና የምሕረት (የተስፋ) ቃሎችን አጣምረው የያዙ ከመሆናቸው ባሻገር በቀጣዩ አዲስ ኪዳን ተፈጻሚ የሚሆኑ በርካታ ትንቢቶችንም አካተው የያዙ ናቸው። ከሁሉም በላይ ያ የመጀመሪያው ኪዳን (ብሉይ ኪዳን) እንደሚያልፍና ሌላ አዲስ ኪዳን እንደሚተካ የተናገረውን መጥቀስ ይቻላል። ይህም እግዚአብሔር በእስራኤላውያን በኩል ለዓለም ያዘጋጀው እቅድ በእስራኤላውያን አለመታዘዝ ሊሳካ ባለመቻሉ በአሮጌው ኪዳን ምትክ ሌላ አዲስ ኪዳን እንደሚገባ በዚያው በብሉይ ኪዳን ዘመን ተናገረ።
« እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን ምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር
ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦
ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። »  
ኤር ፴፩ ፣ ፴፩ - ፴፬
እንግዲህ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ቃል ኪዳን ያከበረ ቢሆንም እስራኤላውያን ግን ኪዳኑን ባለማክበራቸው ያ ቃል ኪዳን ሊጸና አልቻለምና ብሉይ (ያረጀ) ተብሎ አለፈ፤ ይህም አዲስ ቃል ኪዳን  በማለቱ አዲስ የሚለው ቃል የመጀመሪያውን ብሉይ (አሮጌ) እንዲሆን አድርጎታል።
«ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።…. አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ »  ዕብ ፯፣ ፯ና ፲፫።
እዚህ ላይ ብሉይ ኪዳን ብሉይ (አሮጌ/ያረጀ) መባሉ የማይጠቅም ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል።
እንግዲህ ብሉይ ኪዳን በአጭሩ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር የፈጸመውና በእነርሱ አለመታዘዝ ሊጸና ያልቻለው ቃል ኪዳን ነው ማለት እንችላለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ስለብሉይ ኪዳን ጠቅለል አድርገው የሚናገሩ የሚከተሉትን ጥቅሶችን ማየት ይቻላል።
ነህምያ ፱፣ ፯ - ፴፩- በነህምያ ዘመን በሌዋውያን ጸሎት
የሐዋ ፮፣ ፩ -፶- በእስጢፋኖስ ትምህርት
ዕብራ ፲፩፣ ፬ - ፵ - በጰውሎስ ትምህርት
ብሉይ ኪዳንን በዚህ መልኩ አጠቃላይ ታሪካዊ ዳሰሳውን ካየን ወደፊት በምናጠናበት ጊዜ እያንዳንዱ ክፍል ስለምን እንደሚናገር በቀላሉ እንረዳዋለን ማለት ነው።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በሚቀጥለው ክፍል እንዲሁ የአዲስ ኪዳንን ጠቅለል ያለ ታሪካዊ ዳሰሳ እንመለከታለን።
ይቆየን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment