ከአሁን ቀደም
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የብሉይ ኪዳንን ዳሰሳ በየክፍሎቹ ማለትም በኦሪት፣በታሪክ፣ በቅኔና መዝሙራት እንዲሁም በትንቢት ክፍል
ይዘታቸውን በአጭር በአጭሩ ማየታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ በአዲስ ኪዳን ያሉትን ክፍሎች ማለትም የወንጌል፣ የታሪክ፣ የመልእክትና
የትንቢት ክፍሎችን እንዲሁ በየተራ እንዳስሳለን። ለዛሬ የወንጌል ክፍልን እናያለን።
የወንጌል ክፍል
የሚባሉት አራቱ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ እንደሆኑ ይታወቃል። ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው? ስንል ወንጌል ማለት የምሥራች
ማለት ነው። በኃጢአት ለተያዘው የሰው ዘር መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን…መሞቱን እና መነሳቱን የሚገልጽ የደስታ ቃል ማለት
ነው። ከአንድ ወንድሜ እንደተማርኩት ወንጌል ማለት የምስራች መሆኑን ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚተረጉምልን እነዚህን ሁለት ጥቅሶች
ማየት እንችላለን።
አስቀድሞ በነቢዩ
በኢሳይያስ ስለ ክርስቶስ የተነገረው እንዲህ ይላል።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ» ኢሳ ፷፩፣፩-፪
ይህንኑ ክፍል
ሉቃስ በወንጌል ሲጠቅሰው እንዲህ ይላል።
« የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ
ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም
ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።» ሉቃ ፬፣ ፲፯-፲፱።
ነቢዩ ኢሳይያስ
የምስራች ያለውን ወንጌላዊው ሉቃስ ወንጌል ብሎ ይተረጉመዋል። ስለዚህ ወንጌል ማለት የምሥራች
ማለት ነው። ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው የምሥራች ወንጌል ነው። እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወንጌል ማለት ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያብራራል።