Tuesday, April 18, 2017

የትንሣኤው መልእክት


«ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤» ዮሐ ፲፩፣፳፭

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ቀዳሚ ዓላማ ለሕይወት እንደሆነ ራሱ ባለቤቱ ይነግረናል። አዳም ከሕይወት ወደ ሞት አወረደን፤ ክርስቶስ ከሞት ወደ ሕይወት አሻገረን።

«ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።» ፩ ቆሮ ፲፭፣፳፪

ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነኝ ሲል ሙት የሚያስነሳ /በአልአዛር/ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሞቶ ስለተነሳም ጭምር ነው። ሙት ማስነሳት ለአገልጋዮቹም በጸጋ ሊሰጥ ይችላል፡ ሞቶ መነሳት እና በመጨረሻም ሌሎችን ከሞት ማስነሳት የእርሱ ብቻ ሥልጣን ነው። «ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።» ዮሐ ፮፣፵። ስለዚህ ሙት ስላስነሳ፡ ሞቶ ስለተነሳ፡ እና የሚሞቱትን በመጨረሻ ስለሚያስነሳ ትንሣኤ ነኝ አለ። ከትንሣኤ በኋላም ሕይወት ነው።

የትንሣኤው አስፈላጊነት

፩. የሞት መድኃኒት

ሞት ለዘመናት አስፈሪ ሆኖ የኖረ፡ ሁሉንም የሰው ዘር የተቆጣጠረ፡ መፍትሔ ያልተገኘለት የሰው ሕይወት ፍጻሜ ነበር። የዓለም መንግሥታት ስለሞት ለመነጋገር አጀንዳ ይዘው አያውቁም፡ ተመራማሪዎች የሞትን መድኃኒት ለመፈለግ ጥናት አድርገው አያውቁም። ሞት ሁሉንም ዝም ያሰኘ፡ ሁሉንም ጠቅልሎ የገዛ የምድራዊው ኑሮ የመጨረሻው ባለሥልጣን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ግን ለሞት መድኃኒት ተገኘ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገው በሌላ በምንም ነገር ሳይሆን በሞቱ መሆኑ ያስገርማል። ሰው በቁሙ በሕይወት እያለ ብዙ ታላላቅ ነገሮችን ሊሠራ ይችላል። ከታመመ ምናልባት ጥቂት ነገሮችን ይሠራል። ከሞተ በኋላ ግን አንዳች ነገር ሊሠራ አይደለም ሊንቀሳቀስ አይቻለውም።

በሟቹ በኩል ስናየው ሞት የሰው ልጆች የመጨረሻው ደካማ ባሕርይ፡ ምንም ሊሠራበት የማይችል ነው። በቋሚዎች በኩል ስናየው ደግሞ ሞት የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ የመጨረሻው ኃይለኛ ጉዳይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ኃያል የሆነውን ሞትን ድል ያደረገው በጣም ደካማ በሆነው ባሕርያችን በሞት ነው። እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በድካማችን ኃያሉን ጠላታችንን ሞትን ድል አደረገው። «ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና»  ፩ቆሮ ፩፡፳፭። የተባለው ለዚህ ነው።




፪. የክርስትና /የእኛም/ ሕያውነት

 ኢየሱስ ክርስቶስ ባይነሳ ኖሮ /ሞቶ ቀርቶ ቢሆን/ ምን ችግር አለበት?

ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብለከታችን ከንቱ ነው… እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤….እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። ፩ ቆሮ ፲፭፣ ፲፬ - ፲፯

ክርስቶስ ባይነሳ ኖሮ ክርስትና ተረት ሆኖ ይቀር ነበር። ወይም የአንድ ወቅት የታሪክ ክስተት ብቻ ይሆን ነበር።  እንደሌሎች ታዋቂ ሰዎች «አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ሰው ነበረ። ይህን አደረገ፡ በዚህ ወጣ በዚህ ወረደ፡ በመጨረሻ ሞተ፤» ተብሎ ያበቃ ነበር። ብዙ ታላላቅ ሰዎች መጨረሻቸው ሞተ፡ ተብሎ ተጠናቆአል። የክርስቶስ ግን ከነዚህ ይለያል።

ክርስቶስ ባይነሳ ኖሮ መዳናችን አይፈጸመም ነበር። የኃጢአታችን ዋጋ የተከፈለው በሞቱ ሲሆን ሕይወታችን የተረጋገጠው ደግሞ በትንሣኤው ነው። እኛ በዚህ /በሞቱና በትንሣኤው/ ስናምን የመዳናችን ማረጋገጫ ይሰጠናል። ትንሣኤው የክርስትናም የእኛም ሕያውነት ነው።

፫. የመጨረሻው ዘመን ትንሣኤ /ትንሣኤ ዘጉባኤ/

አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ፩ ቆሮ ፲፭፣፳

የክርስቶስ ትንሣኤ የኛም ትንሣኤ ማረጋገጫ ነው። እርሱ በኩራት /መጀመሪያ/ ሆኖ በመነሳት አሳይቷል። በፍጻሜ ዘመን ሁሉም ሰው ከሞት ይነሳል፤ ግን በሁለት መንገድ። ጌታም አለ፡-

…በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና…። ዮሐ ፭፣፳፰

አባቶች ይህን ትንሳኤ ዘለክብር እና ትንሣኤ ዘለሃሳር ብለው ያስቀምጡታል።

በመጨረሻ ዘመን ከሞት መነሳት የሁሉም ሰው ግዴታ ነው። የምንነሳው ለምን ዓይነት ሕይወት ነው የሚለው ነው ልዩነቱ። ይህም የሚወሰነው አሁን በዚህ ምድር በምናደርገው ምርጫና ውሳኔ - በትንሣኤው ጌታ በክርስቶስ በማመን እና ባለማመን ነው።

«ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤…» ዮሐ ፲፩፣ ፴፭

፬. የአማኞች የየዕለት ትንሣኤ

ኢየሱስ ክርስቶስን በየጊዜው ያሳደዱት በመጨረሻም ለሞት የዳረጉት የእግዚአብሔር ነን የሚሉት አይሁድ መሆናቸው ይገርማል። ዛሬም በእውነት ክርስቶስን ያመኑ፡ ክርስቶስን የሚሰብኩ በእግዚአብሔር ሰዎች ቢሰደዱ አይገርምም፡፡

በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ፪ ጢሞ ፫፣፲፪

 ኢየሱስ ክርስቶስን በመስበካቸው ስም እየተሰጣቸው በየቀኑ በሚደርስባቸው ስደት እና ስም ማጥፋት በመንፈሳቸው ስለሚጎዱ እንደተገደሉ ይቆጠራሉ። «ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። » ሮሜ ፰፣፴፮።  ነገር ግን የትንሣኤው ኃይል ስላለ እንደገና በመንፈሳቸው ይነሣሉ። በክርስቶስ ምክንያት በየቀኑ የምንገደል ከሆነ በየቀኑ እየተነሳን ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ የትንሣኤው ነገር አንድ ሰሞን የሚዘከርና የሚያበቃ ጉዳይ ሳይሆን በዕለታዊ ኑሮአችን ትልቅ ስፍራ ያለው የሚያኖረን ኃይል ነው ማለት ነው።

፭. የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር ዘላለማዊነት

ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ስሙ አማኑኤል ተብሎ ሲጠራ ትርጓሜው «እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ» ማለት ነው። /ማቴ ፩፣ ፳፫/ ። ክርስቶስ ሲወለድ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ሲሞት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን አቆመ ማለት ይመስላል። ይሁን እንጂ ሞቶ ስላልቀረ /ስለተነሳ/ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ቀጥሏል። ለዚህ ነው ከትንሣኤው በኋላ ለደቀመዛሙርት፡-

እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። ያለው ማቴ ፳፰፣ ፳

ስለዚህ ዛሬ ክርስቶስ በአካል በምድር የለም፤ በአካሉ በቤተ ክርስቲያን /በእኛ/ ግን ይሠራል።

የትንሣኤው መልእክት

ባለፈው ጽሑፍ እንዳየነው ፬ቱም ወንጌላውያን አጀማመራቸው እና አካሄዳቸው ቢለያይም አጨራረሳቸው ተመሳሳይ ነው - የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በዝርዝር ዘግበዋል።

በ፬ቱም ወንጌሎች ጌታ ከተነሳ በኋላ ለሁሉም ሐዋርያት ያስተላለፈው አንድ ትዕዛዝ ነው።

እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤…..ማቴዎስ ፳፰፣ ፲፱

እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ

ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።… ማርቆስ ፲፮፣ ፲፭-፲፮

በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።....ሉቃስ ፳፬፣ ፵፯-፵፰

..ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።… ዮሐንስ ፳፣ ፳፩-፳፫

ይህ በተለያየ አገላለገጽ የቀረበው አንድ ትእዛዝ የትንሣኤው መልእከት ስብከተ-ወንጌል ነው።

-      ትንሣኤ በወንጌል መጨረሻ ቢጠቀስም የወንጌል ሥራ ግን መጀመሪያ ነው። ሐዋርያት ይህን ታላቅ አደራ እስከመጨረሻው ተወጥተዋል። ሌላው ቀርቶ አገልግሎታቸውን ከትንሣኤው ምስክርነት ጋር በመሰየም ይንቀሳቀሱ ነበር። /የሐዋ ፩፣፳፪ ፤ ፪፣፴፪፤ ፫፣፲፭፤ ፬፣፴፫…/

-      ወንጌልን የምስራች ያሰኘው ትንሣኤ ነው። የወንጌል ትርጉም ራሱ የጌታን ሞትና ትንሣኤ መመስከር ነው።  / ፩ቆሮ ፲፭፣ ፩ - ፫/

-      ሞት የሁሉም ፍርሃት ነው፣ ሞትን ግን መድፈር የሚቻለው የትንሣኤው ትርጉምና ኃይል ሲገባን ነው። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ፊልጵ ፩፣ ፳፩

ሞት ለሁሉም ሰው ጉዳት ነው፤ ሞት ጥቅም የሚሆነው በክርስቶስ ብቻ ነው።

-      ሰዎች የሞትን ፍርሃት በክርስቶስ እስካላስወገዱ ድረስ አይደለም ሞት ከሞት የሚያንሱት ሌሎች ችግሮች ሁሉ ሲየስፈሯቸው ይኖራሉ። ስለዚህ የሞትና የሌሎችም ሥጋት እንዲወገድ የትንሣኤው መልእክት ወንጌል /የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ/ ሊሰበክ ይገባል።

የክርስቶስ የትንሣኤው መልእክት - ስብከተ-ወንጌልን ማስፋፋት ነው።

ዛሬስ የኛ የትንሣኤው መልእክት ምንድን ነው? ትንሣኤን ስናስብ ትዝ የሚለን ምንድን ነው? በዓሉ / ሥነ ሥርዓቱ…የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ሙሉ ጊዜ መድቦ ማሰቡ መልካም ነው። 

ትንሣኤን የአንድ ወቅት ሥርዓት ብቻ አድርጎ ማሰብ ያለው ችግር ምንድን ነው? ቢባል

በሌላ ጊዜ እንዲረሳ፣ ትኩረት እንዳይሰጠው ያደርጋል፤ በበዓሉ ወቅት ካለው የመብል ሽር-ጉድ የተነሳ ዓላማውን በመሳት ምግብ-ተኮር በዓል ያደርገዋል። ከዚህ የሚብሰው ደግሞ በትንሣኤው ስም የሚካሄዱ የኃጢአት ግብዣዎች ናቸው። ትንሣኤውን የኃጢአት ትንሣኤ ያስመስለዋል። ይህም እየታየ ያለ እውነታ ነው። ታዲያ ይህ አካሄዳችን እስከመቼ?

እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።  ቆላስ ፫፣ ፩-፪

በትንሣኤ የሚታረደግ በግ ወደ ቤታችን ከማስገባታችን በፊት /ጋር የታረደውን በግ ወደ ልባችን ማስገባታችን እናረጋግጥ። ያኖረን እና የሚያኖረን የእግዚአብሔር በግ ነውና።

ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።» ራእ ፩፣፭-፮።

ዲ/ን ኢንጅነር አብርሃም አብደላ ቅዳሜ ሚያዝያ ፳፪፣ ፳፻፰ ዓ/ም - ጎንደር

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment