Thursday, April 2, 2015

ሕጉን/ቃሉን/ ማሰብ


የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።  ኢያ ፩፣ ፰
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። …. የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።   መዝ ፩፣ ፩ - ፫
-      እግዚአብሔር ከሙሴ በኋላ ላስነሳው መሪ- ለኢያሱ- ከ፪ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለሚመራው፣ ከነዓንን ለማውረስ ላዘጋጀው ሰው ያስታጠቀው መሣሪያ - ቃሉን እንዲያስብ ነው።
o   የሚመራው ቀላል ሕዝብ አይደለም። በጉዞ የታከተው…
o   ከነዓን ምድሪቱ በአሕዛብ እጅ ስለሆነች ጦርነት አለበት።
፩. ሕጉ ምንድን ነው? –
የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ነፍስን ይመልሳል።  መዝ ፲፰/፲፱፣ ፯
ሕጉ፡- ፍጹም - እንከን የለሽ ነው። ሕጉ ለሰዎች የተሰጠ ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች የሚፈልገውን የቅድስና መስፈርት ያሳያል። ወይም ለእግዚአብሔር ቅድስና ሰዎች መስጠት ያለባቸውን ምላሽ ያስቀምጣል።
ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው /መኖር የሚፈልገው ሰው እንደ እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለበት እንከን የለሽ መሆን አለበት።
ይህን ደግሞ ማድረግ ለሰው አልተቻለውም። በሕጉ መጽደቅ / በእግዚአብሔር ፊት የመቆም ብቃት ማግኘት/ አልተቻለም።
ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው። ሮሜ ፫፣ ፳።
ሕጉን መሥራት/መፈጸም ባንችልም - ማሰብ ግን አለብን።
-       ሕጉን የምንፈጽመው በትዕዛዝ ግዳጅ - ሳይሆን በፍቅር መንፈስ ነው።
-       ፍቅር - የእኛ ጥረት ውጤት ሳይሆን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሚገልጸው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። --  ገላ ፭፣፳፪ - ፍቅር ከ፱ኙ የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። 
-       ሕጉን የምንፈጽመው በክርስቶስ ስንሆን እና በመንፈስ ቅዱስ የፍቅር ሰዎች ስንሆን ነው።
የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።   ሮሜ ፲፣ ፬
ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።  ሮሜ ፲፫፣ ፲


፪. አሳብ ምንድን ነው?
-      አሳቢነት - ከነፍስ ፫ ባሕርያት አንዱ፣ ከእንስሳት የምንለይበት፣ እግዚአብሔርን የምንመስልበት። ነፍስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ስለሆነች።
-      ነፍስ፡- አሳቢነት፣ ተናጋሪነት፣ ዘላለማዊነት - - በአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የተመሰለች።
-      በተፈጥሮዋ -የእግዚአብሔር እስትንፋስ ለሆነችው ነፍስ- የሚስማማት የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉና እስትንፋሱ ይስማማሉና።
-      አሰባችን - ቃላችንን እና ተግባራችንን - ይወስናል/ይመራል።
-      የሁሉም ድርጊቶች መነሻ አሳብ ነው፡ - የአሳብ ኃጢአት ሁለት ዓይነት ናቸው፡-
፩. ምኞት፡- ከ፲ቱ ትዕዛዛት ፲ኛው። እግዚአብሔር ኃጢአትን ድርጊቱ ከተከናወነ በኋላ ሳይሆን በአሳባችን ስንወስን ነው ኃጢአት ብሎ የሚይዘው። ጌታ በወንጌል እንደተናገረው፡-
«አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።»   ማቴ ፭፣ ፳፯ - ፳፰
ሁሉም ኃጢአት መነሻው ምኞት ነው። መድረሻው ሞት ነው።
«ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።»  ያዕ ፩፣ ፲፬-፲፭
፪. ጭንቀት፡- የእምነት ማጣት/መጉደል ነው። ስለነገ መጨነቅ። ጌታ አትጨነቁ ብሏል፡
«ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።»  ማቴ ፮፣ ፴፬
«በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።»   ፊልጵ ፬፣፮
-       ጭንቀት - እእምሮአችን በሌላ ነገር እንዲያዝ ስለሚያደርግ እግዚአብሔርን፣ ቃሉን፣ ፍቅሩን፣ ታማኝነቱን እንድንዘነጋ ያደርጋል። - በራሱ ኃጢአት ባይባልም የኃጢአት በር ነው።
፫. ቃሉን ማሰብ ያለብን እንዴት ነው?
-      ቃሉን በደንብ፣ በጥሞና፣ በማስተዋል ማንበብ አለብን። ሁለት ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች አሉ ይላሉ ምሑራን፡-
o   ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ፡- የሆነ አሳብ ይዘን ያን የሚደግፍልን አሳብ መፈለግ። ወይም እንደገባን በማሰብ ማንበብ።
o   ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ፡- በንጹሕ አእምሮ፣ ነጻ ሆነን ማንበብ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለራሱ ይናገር እንደተባለው።
-      ዝምብሎ ማንበብ ብቻ አይደለም። አንብቦ ዘወር ማለት/መርሳት አይደለም።
- ቃሉ ከእንደበትና ከአእምሮ በላይ በልባችን እንዲሆን ይፈልጋል።
ቃሉ ወደ ልባችን የሚገባው በ፫ቱ የስሜት ሕዋሳት ነው።
- ዓይን - በማየት፣  አፍ- በማንበብ ፣ ጆሮ- በመስማት
- እያየን እናነባለን - ስናነብም ይሰማናል። ይህን በተደጋጋሚ ማድረግ። በማስተዋል ማንበብ። ወደ ውስጣችን እስኪሰርጽ - ሙሉ አሳባችን እስኪቆጣጠር ድረስ።
-      ሰይጣን አንዱ ስራው ቃሉን ከልባችን መውሰድ ነው። ይህን የሚያደርገው እኛን በሌላ ነገር በመጥመድ ነው፡፡-  በዕለት ተዕለት ጉዳዮች፡- በኢንተርኔት፣ በጨዋታ፣ በዋዛ፣ በቀልድ….
የዘሪው ምሳሌ፡-
የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። -   ማቴ ፲፫፣ ፲፱
፬. ቃሉን ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
፬- ፩. በአቋም ለመጽናት
    አእምሮ፡- ባዶ ሊሆን አይችልም።
-      በዚች ምድር ላይ ባዶ ስፍራ /Vaccum/ የለም። ባዶ የሚመስለን እንኳ በአየር ተሞልቷል። አእምሯችን በሌላ ነገር ከሚሞላ በቃለ እግዚአብሔር ቢሞላ መልካም ነው።
-      ውሎአችንን መጠንቀቅ አለብን፣ በምናያቸው በምንሰማቸው ጉዳዮች መሰረት አእምሯችን ይያዛል/ ይጠመዳል።
-      ውሳኔያችንን ሁሉ የሚያስቀለብስ ጉዳይ ሊገጥመን ይችላል። ያየነውን/የሰማነውን መሆን/መስራት ያምረናል።
o   ለምሳሌ ሯጮች «ሲሳካላቸው» - ብዙ ሰው ጧት ጧት ዱብ ዱብ ሲል ነበር።
ቢዝነስ ሰው ስናይ - ያን ቢዝነስ ለመስራት እንፈልጋለን…..
-      በሕይወታችን አቋም/ ራእይ ሊኖረን ይገባል። ያየነው የሚያምረን፣ አስር ጊዜ የምንገላበጥ ከሆነ አንዱንም ሳንይዝ እንቀራለን።… በርግጥ ዕቅድ መሻሻል ይችላል/ አስር ጊዜ ግን መቀያየር የለበትም።
-      ራእይ ካለን - በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመሰረተ እና እግዚአብሔርን የሚያስከብር - ጉዟችን ቀጥታ ይሆናል። ወደ ግራም ወደ ቀኝም አንልም። - ለኢያሱ እንዳለው፡-
o   በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።  ኢያ ፩፣ ፯
፬-፪. ከክፉ ለመጠበቅ - መልካም ለማድረግ
ቃሉን የምናስበው፡- ከክፉ ምኞት ለመጠበቅ - ከዚያም - መልካም ለማድረግ ነው።
-      አእምሮን የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም፡
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።
አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤   ፊልጵ ፬፣ ፯ - ፰
፬-፫. የሥራ መከናወንን ለማግኘት
-      «ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።
እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።»  መዝ ፩፣ ፪ - ፫
-      ሥራን ማቀድ፣ መሥራት ይቻላል። መከናወንን የሚሰጥ ግን እግዚአብሔር ነው። ሐዋርያት ከጌታ ትንሣዔ በኋላ ዓሳ ለማጥመድ ሌሊቱን ሙሉ ደከሙ። - አንዲት አሳ አልያዘም።
--- ልምድ ያላቸው፣ ባሕሩን የሚያውቁት፣ ፯ ሆነው፣ ለረጅም ሰዓት።
n በክርስቶስ በቃሉ መሠረት - አንድ ጊዜ በቀኝ በኩል ቢጥሉት - ፻፶፫ ትላልቅ ዓሳ ያዙ።
n እንደቃሉ - መረቡን መጣል የእኛ ሥራ ነው። ዓሳዎችን ወደ መረቡ ማስገባት ግን የአምላክ ስራ ነው።
-      የቀለም ትምህርት ስንማር ለጊዜው ለፈተና፣ ብቻ ይሆናል፤ በኋላ እንረሳዋለን።
የእግዚአብሔር ቃል ግን የዘላለም ጉዳይ ስለሆነ ሁልጊዜ አብሮን ሊኖር ይገባል። በልባችን/በአሳባችን። የአንድ ወቅት አጀንዳ/ጉዳይ - ዜና አይደለም። ሕይወት ነው።
-      ዕለት ዕለት የሚገጥሙንን ጉዳዮች ከቃሉ አንጻር ለመመዘን ቃሉ ሁልጊዜ በልባችን ሊሆን ይገባል። ሰይጣን ጌታን ሲፈትነው ቃሉን እየጠቀሰ ነበር። ጌታም ሲመልስለት ቃሉን እየጠቀሰ ነበር። ሁለቱም መጽሐፍ አልያዙም። - በቃላቸው ነበር።
ለኢያሱ፡- የሙሴ ምትክ መሪ፣ አገር ለመምራት/ ለማውረስ፣ ጦርነት ድል ለማድረግ…. እግዚአብሔር ያስታጠቀው - ቃሉን- ብቻ ነው።
፭. ቃሉን ለማሰብ ያለን ዝግጁነት
-      እግዚአብሔር ለኢያሱ ያለው፡- በቀንም በሌትም - ዘወትር  ያለማቋረጥ ማለት ነው።
ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው። ኢያ ፩፣ ፰
-      ቃሉን ለመጠበቅና ለማድረግ - የሚያስፈልገው አንድ ብቸኛ ነገር - ማሰብ -  ነው።
-      ምክንያቱም፡- አሳባችን ቃላችንንና ተግባራችንን ይመራልና። ለማሰብ ምን እናድርግ?
፭-፩ ቃሉን ለማሰብ - ማንበብ/መስማት አለብን
-      እኛ ለቃሉ ምን ያህል ጊዜ መድበናል? -- ለማንበብ፣ ለመስማት፣ ለማየት።
በሳምንት ስንት ቀን? -  በቀን ስንት ሰአት?
 በቃሉ የምናድገው በተሰጠንበት መጠን ነው።
በቀድሞ ዘመን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እደሉ አልነበራቸውም። ለመስማት ወደ  ምኩራብና ቤተ መቅደስ መሄድ ነበረባቸው። 
በአሁኑ ሰአት ቃሉ /መጽሐፍ ቅዱስ/ ከቀድሞው ዘመን በተሻለ ወደየቤታችን ገብቷል። ከዚያም አልፎ ወደየሞባይላችን /ታብሌታችን/ ገብቷል። አብሮን ይሄዳል። ሰፊ ዕድል አለ።
ታዲያ ምን ያህል ጊዜ ሰጥተን ለማንበብ ዝግጁዎች ነን? - ቃሉ ቀርቦልን እኛ ከራቅን የራሳችን ችግር ነው የሚሆነው።
፭. ፫ ቃሉን ለማሰብ - ወደ ውስጣችን ማስገባት   የሰማነውን/ያነበብነውን
-      ቃሉ እንደ ምግብ ተቆጥሯል።
-      ለሰውነታችን የምንመገበው ምግብ፡- ከሰውነታችን ጋር ይዋሃዳል። በሠራ አካላታችን- ወደ ሁሉም የሰውነት ክፍሎቻችን ይሰራጫል /በደም/ ። ይዋሃደናል።
o   ለውጥ/ውጤት ያመጣል። - በወዝ/ በውፍረት/ በቁመት/ በዕድገት…
-      ለነፍሳችንም የምንመገበው ቃሉ እንዲሁ ወደ ውስጣችን ሊዋሃደን ይገባል። -እንደ ምግብ፣-
o   እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ።
አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ።
እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።   ሕዝ ፫፣ ፩ - ፫
-      ከበላን፣ ከተስማማን በኋላ ወደ ውጭ ይገለጻል። -- ብላ-- ተናገር። ቀጣዩ፡-
፭-፪ ቃሉን ለማሰብ - መናገር / መስበክ/ማውራት አለብን   - ወደ ውስጣችን የገባውን
-      ለኢያሱ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎታል፡-
o   የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥   ኢያ ፩፣ ፰
-      አውራው .. ተጫወተው.. ማለት ነው።
-      እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሎ አዟል።
      እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ።
ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛምስትነሣም ተጫወተው።
     በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ።
በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።   ዘዳ ፮፣ ፮ - ፱
-      በሁሉም የሕይወት ክፍላችን/ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን.. ቃሉን ማሰብ።
-      የምንናገረው የምናስበውን ነው። አንድን ነገር በተናገርነው መጠን ይበልጥ እያሰብነው እንሄዳለን። ምክንያቱም ለምንናገረው ነገር እናስባለንና።

ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል - በየጊዜው በሁሉም ቦታና ሁኔታ - ማሰብ - ትልቅ ኃይል ያለው የሥራችን ሁሉ መከናወን የሚገኝበት በቀላሉ ልንፈጽመው የምንችል ስለሆነ መለማመድ አለብን።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment