Friday, July 13, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ - ወንዞችና መልክአ-ምድሮች


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከእምነትና ከምግባር ቀጥሎ መረጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጥቀስ ባለፈው ሃገሮችና ከተሞች በሚል ጠቅለል አድርገን አይተን ነበር። ለዛሬ የወንዞችና መልክአ-ምድሮችን አስፈላጊነት በምሳሌ እናያለየን፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት ገነትን አጠጥቶ የሚወጣው ወንዝ ከአራት እንደሚከፈል ተጽፎአል።
« ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፣ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።» ዘፍ ፪፣፲
ለመሆኑ ገነት የሚባለው የዚያን ጊዜ የት ነበር? አሁንስ የትኛው ነው? አራቱ ወንዞች ዛሬ የትኞቹ ናቸው? መረጃ ያስፈልገናል ማለት ነው።
ቃኤል አቤልን  በሜዳ ገደለው፣ ሎጥ ወደ ተራራ ሸሽቶ አመለጠ፣ ለምን ወደ ሜዳ ወሰደው?  በሜዳ ያለ ሰው እና የሚያደርገው ነገር ለሁሉም የሚታይ ስለሆነ መሸሸግም ሆነ ማምለጥ አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የመጀመሪያው ነፍሰ-ገዳይ ቃኤል የፈጸመው በደል እንኳን ከእግዚአብሔር ከሰው የተሰወረ አልነበረም። ተራራ ግን ራስን ደብቆ ሌላውን ማየት የሚቻልበት ስትራቴጂያዊ ቦታ ነው። ሎጥ እና ሌሎችም ወደ ተራራ ሸሽተው ሲያመልጡ በመጽሐፍ ቅዱስ እናያለን።
 እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ተከፍሎ በደረቅ እንደተሻገሩ በመጽሐፍ ቅዱሰ የተገለጸ ታላቅ ተአምር ነው። እዚህ ላይ አንድ ወንድሜ የነገረኝ ቀልድ አዘል ቁም ነገር ትዝ አለኝ። ሁለቱ ጓደኛሞች አንዱ በእግዚአብሔር የሚታመን፣ ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያመሰግን፤ አንደኛው ግን ሁልጊዜ በቀልድና በፌዝ ጊዜውን የሚያባክን ነበሩ። ታዲያ የመጀመሪያው አምላኩን ሲያመሰግን እስራኤላውያንን ቀይ ባሕርን ከፍለህ ያሻገርህ አምላኬ ተመስገን፡ ተመስገን እያለ ይዘምራል። ያመስግናል።  ፈዘኛ ጓደኛው፡- አንተ ቀይ-ባሕር፡ ቀይ ባሕር ትላለህ የዚያን ጊዜ የነበረው ቀይ ባሐር በአሁኑ አንድ ኩሬ የምታክል ውሃ ነው የነበር አለው። በዚህ ጊዜ መንፈሳዊው ይህን ሲሰማ ይበልጥ እያመሰገነ ይፈነጥዝ ጀመር። እንዴ ምነው? እንደዚህ ስላልኩህ ይበልጥ ፈነጠዝክ ቢለው አምላኬ ፈርኦንንና ሠራዊቱን ኩሬ በምታህል ውኃ ማስጠሙ አስገርሞኝ ነው አለው ይባላል። የፈለገ ነገር ቢሰማ ሳይበገር ሁሉንም ነገር ለአምላኩ ክብር አዋለው።
በዚያን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹት ቀይ-ባሕር፡ ዮርዳኖስ ወንዝ ዛሬ የትኞቹ ናቸው? ምን ይመስላሉ? የሚለውን ማወቃችን መጽሐፍ ቅዱስንና የአምላክን ተአምራት በይበልጥ እንድንረዳ እርሱንም እንድናመሰግን ይረዳናል።


መልክአ-ምድሮች የእግዚአብሔርን ቸርነት ይመሰክራሉ። የጽዮን ተራራ በኢየሩሳሌም ዙርያ ከሚገኙ ተራሮች የምትገኝ ዳዊት የተቆጣጠራትና ታቦተ-ጽዮንን ያስቀመጠባት፣  የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ-መቅደሱን የተሰራባት፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቦታ የሚገኝ ተራራ ነው።
« እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን። »
ስለጽዮን ተራራ ስናውቅ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ያደረገላቸውን ፍቅር፣ እንክብካቤ ይበልጥ እንረዳለን። የእስራኤላውያን ምድረ-ርስት ኢየሩሳሌም በጽዮን ተራራ መሆኗ በጦርነት ወቅት ለመሪዎች ያለውን አስፈላጊነት በቀላሉ በኛ ሃገር ምሳሌ ማየት ይቻላል። ብዙ የሃገራችን ቀደምት ነገሥታት  ከተሞቻቸውን በተራራ እንደመሠረቱ የጎንደሩን አጼ ፋሲልና፡ የአዲስ አበባውን አጼ ምኒልክ መጥቀስ ይቻላል።
ተራሮች በምሳሌያዊ አስተምህሮዎቻቸው በእርሱ የሚታመኑ እንደማይወድቁ በመግለጽ የእግዚአብሔርን ፍቅርና እንክብካቤ ያሳያሉ።
« በእግዚአብሔር የታመኑ እንደማይታወክ ለዘላለም እንደሚኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው።  ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ሆኑ፥ ከዛሬ ጀምሮ ለዘላለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው። »  መዝ ፻፳፭፣፩-፪
በሕገ-ልቦና የነበሩ የብሉይ ኪዳን አበው መስዋዕታቸውን በተራራ ያቀርቡ ነበር። ከፍ ያለ ቦታ ስለሆነ የአምልኮ መግለጫ ነበር። ሙሴ የሕገ-ኦሪት መሰረት የሆነውን ትእዛዙን የተቀበለው፣ ለሕዝቡም ያስተላለፈው በሲና ተራራ ነበር። በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከት፡ ሙሴ በሕገ-ኦሪት ከሰጠውና ከዓለሙ የመልካምነት መስፈርት የሚበልጥ፡ የከፍታ ሕይወትን የሚገልጽ ትምህርት አስተማረ።
« ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ » ማቴ ፭፣፳፩-፳፪።
በተራራ ማስተማሩ ከብሉይ ኪዳኑም ከዓለሙም የተሻለ ከፍ ያለ የቅድስና ሕይወት እንዲኖረን ሲሆን እርሱ ከፍ ብሎ ማስተማሩ ሁሉም እንዲያዳምጡት፡ እርሱም ክብሩ ከሁሉም ከፍ ያለ መሆኑን እንዲረዱ ወዘተ… ነው።
መልክአ-ምድሮች ከቀጥተኛ አገልግሎታቸው በተጨማሪ በተምሳሌታዊ አነጋገር ተራራ እንደ ትዕቢት በመቆጠሩ ዝቅ ይበል፣ ሸለቆውም እንደ አጉል ትሕትና በመቆጠሩ ይሙላ ተብሏል።
« የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።  ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል። » ኢሳ ፵፣፫-፬።
የአዋጅ ነጋሪ ቃል መጥምቁ ዮሐንስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ - ለአምላካችን ጎዳና- መንገድ ጠራጊ ተብሎ የተነገረለት የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ነቢይ፣ የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ሐዋርያ፡ አንዲሁም ባሕታዊና ሰማዕት ነበረ። በንስሐ ስብከትና ጥምቀት ሰዎች ለታላቁ አገልግሎት ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አንዲዘጋጁ አደረገ።
እንግዲህ ወንዞችና መልክአ ምድራዊ ገጽታዎች በቀጥታም ይሁን በምሳሌ የእግዘኢብሔርን ቸርነት፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንድንረዳ ያላቸውን ጠቀሜታ ቀላል የሚባል ስላልሆነ ስለነርሱ ማወቅ አስፋለጊ ጉዳይ ነው ማለት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ቀደም ብለን የጠቀስናቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ  ባሕሎች፡ ገንዘቦች፡ እንስሳት፣ ትውልዶች፣ የዘር ሐረጎች፣ ጸሐፊዎች ፣አጻጻፍ እና የአነጋገር ዘይቤዎች፣ የመጻሕፍቱን ቅደም ተከተል፣ ሥርዓተ ነጥቦች፣ ጥሬ ቃላት ወዘተ… መረጃ ማግኘታችን ለጥናታችን አጋዥ እንደሆነ ቀደም ብለን ያየናቸው ምሳሌዎች ያስረዱናል። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ አንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሲገጥሙን ቆም ብለን ስለእነርሱ ዝርዝር መረጃ፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ-ቃላት ከሌላም ማጣቀሻ በመፈለግ ስንረዳ መልእክቱ ግልጽ ይሆናልናል። ብዙ ትምህርትም እናገኝበታለን።    
በአጠቃላይ እስከአሁን እንደመግቢያ ያየነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በቅድሚያ ማወቅ የሚገቡንን፡-
-      እምነት፡- ስለእግዚአብሔርና ስለኢየሱስ ክርስቶስ በምሥጢረ-ሥላሴና በምሥጢረ-ሥጋዌ፣
-      ምግባር-  ለቃሉ መታዘዝና ጸሎት ማድረግ
-      መረጃ- በሚለው እንደምሳሌ ሃገሮችን፡ ከተሞችን፡ ወንዞችንና ተራሮችን በመጠኑ አይተናል።
ከዚህ በኋላ ወደዋናው የጥናታችን ክፍል እንገባለን። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በሚቀጥለው ትምህርታችን የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ዳሰሳ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን እናያለን።
ይቆየን።

5 comments:

  1. መፅሀፍ ቅዱስ እንደት አሪጌ ማንበብ እንዳለብኝ & ሂወይተን የምሌዉጡ ትምሂርቶች ዎስጃሌሁ & ሰዉ ሁሉ ተምሮ አዉቆ ለአግ/ር መንግሲት እራሱን አንድያዘጋጅ ለምታሬጉ ጥረት እግ/ር ይባርካችሁ።

    ReplyDelete
  2. Egizabhar Yestilen Kala Hiwot Yasemalene.

    ReplyDelete
  3. bible is z life of you.

    ReplyDelete

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment