Saturday, November 8, 2014

ስለጉድለት አልልም - ፪

.......ሰይጣን በጉድለታችን ይፈትነናል። እግዚአብሔር ይህን እያወቀ ለምን ዝም ይላል?
፫. ጉድለታችን ለእግዚአብሔር ምን ያደርግለታል?
እግዚአብሔር ጉድለታችንን ያውቃል። ጉድለታችን፡-
1.     የእርሱ ሙላት መገለጫ
-      የእስራኤልን ሕዝብ ግማሽ ሚሊየን በላይ የመራው ሙሴ ኮልታፋ ሰው ነበረ።
ዘጸ ፬፣፩-፲፫። ሙሴ እግዚአብሔርን ሌላ ሰው ፈልግ፡ ብሎት ነበረ።
-      ከመወለዱ ጀምሮ አይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ሰው በማን ኃጢአት እንደዛ ሆነ?
ዮሐ ፱፣፩-፫። …«የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው። »
የእስራኤል ተወዳጅ ንጉሥ ዳዊት እረኛ የተናቀ.. ለንግሥና ምርጫ የተረሳ ነበረ።
እግዚአብሔር በተናቁ፡ ጉድለት በሚታይባቸው ፣ በጉድለታችን መሥራት ልማዱ ነው።
ክብሩን ለመግለጽ።
ሙላታችን አያግዘውም። ጉድለታችን አያደናቅፈውም። ብቻውን ይሠራል…ብቻውን ክብሩን ይወስዳል።
2.    እርሱ ብቻ እንዲመለክ፡
አዳም አንዲት ዛፍ የከለከለው እግዚአብሔርን እንዳይረሳ/ እንዲያስታውስ ነው።
ሁሉ ነገር ቢሰጠውና ቢፈቀድለት እኔ ከሁሉ በላይ ነኝ ብሎ በትዕቢት እንደሳጥናኤል እንዳይወድቅ።…
-      ሁሉ ነገር ቢሟላልን እግዚአብሔር ይረሳል።
-      ሁሉ ነገር ቢጎድል መኖር አይቻልም።
ስለዚህ እግዚአብሔር ሆን ብሎ ሕይወትን በጉድለት አዋቀራት።
«ጎደሎው የጸሎት ርእስ ነው።» ይባላል። ካለዚያ አምላክን እንረሳለን።
3.    ለኛ ጥቅም ነው።
ከተሰጡን ነገሮች ጋር አንድ አንድ ጉድለት አለ። በዚች ዓለም ፍጹም የሆነ ነገር የለም።
ሰዎች ስንባል ለመያዝ (ያ - ይጠብቃል) የምናስቸግር ፍጡሮች ነን።
እስራኤላውያንን ከግብጽ በታላቅ ተአምራት አውጥቶ በበረሃ መና እየመገበ ሲመራቸው መና ሰለቸን አሉ።  ዘኁ ፲፩፣ ፮
ምድረ ርስትን ለመውረስ ተዘጋጅተው በነዋሪዎቹ ሃያልነት ወሬ በግብጽ ምነው በሞትን አሉ?.... ዘኁ ፲፫ ና ፲፬
ብዙ ጊዜ ችግራችን የተደረገልንን እንረሳለን። እንለወጣለን።….
-      ለመያዝ (ያ - ይጠብቃል) የሚያስቸግሩ ዕቃዎች ማንጠልጠያ ቀዳዳዎች አሉአቸው።
ለትኩስ ሻይ በብርጭቆ ማንጠልጠያ፣ ለጋለ ብረት ምጣድ ጆሮ… አሉአቸው።
መያዣዎቹ ቀዳዳዎች.. ክፍተቶች ናቸው።… ጉድለቶች።
-      እኛም ጉድለቶቻችን መያዣዎቻችን (ያ - ይጠብቃል) ናቸው። እግዚአብሔር እኛን የሚይዝበት።
-      በምድር ሁሉ ቢሞላልንና ፍጹም ሰላምና እረፍት ቢሆን የመንግሥተ ሰማያት ጉዞአችንን እናቆማለን። እንረሳለን። አንድ ወንድም እንዳለው፡-
 ለእግዚአብሔር፡ « በቃ፡ መንግሥተ ሰማያት ምና ምን የምትለውን ተወው. እዚሁ ተመችቶኛል… » እንዳንል።
፫. በተስፋ እንድንኖር  በምድር በመጨረሻም እስከ ሰማይ።
ሕይወት ቀጣይ የምትሆነው በጉድለት ስለተዋቀረች ነው።
ዛሬ ጥረት የምናደርገው ዛሬ የሌለንን ነገር ነገ ለማግኘት ነው።
ዛሬ የምንማረው ነገ ሥራ ለመያዝ ነው።.. ስንይዘውም ከዚያ የተሻለ ሥራ እንፈልጋለን…..
ዛሬ ሥራ ስንይዝ ትዳር እናስባለን።… ትዳር ሲመጣ ልጅ እናስባለን።……
አንዱ ሲሞላ.. ሌላ ጉድለት። ያ ሲሞላ… ሌላ ጉድለት… እያለ ኑሮ ይገፋል።  እስከ ሞት።
-      የዛሬ ጉድለት የሁልጊዜ ጉድለት አይደለም / አይሆንምም።
-      ጉድለት ይሞላል፡ ግን አብሮ ሌላ ጉድለት ይዞ ይመጣል።
የዚች ዓለም መዋቅር እነደዚህ ነው። ከጨለማ ቀጥሎ ብርሃን። ከብርሃን ቀጥሎ ጨለማ።
ጨለማው እንደጨለመ አይቀጥልም።… ይነጋል።
ብርሃኑም እንደበራ አይኖርም። … ይመሻል።
ጨለማው ጉድለታችን የሚያማርረን ሊሆን አይገባም።
ብርሃኑ ሙላታችንም የሚያስጨፍረን አይደለም።
ስለዚህ ሁሉም በልክ ይሁን።
የማያቋርጥ ፍጹም ሰላምና እረፍት በመንግሥተ ሰማያት ብቻ ነው።
ጉድለታችን የዚች ዓለም መኖሪያና መያዣችን የሆነ አምላካዊ ጥበብ ነው።

በጉድለታችን ውስጥ በእግዚአብሔር ደስ ሊለን ይገባል።

No comments:

Post a Comment

አስተያየትዎን ይስጡ / Give Comment