ካሁን ቀደም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በቅድሚያ ማወቅ የሚያስፈልጉን ጉዳዮች እምነት፡ ምግባርና መረጃ በማለት በእምነት
ሥር ስለእግዚአብሔርና ስለክርስቶስ (በምሥጢረ-ሥላሴና በምሥጢረ-ሥጋዌ)፡ በምግባር ሥር ጸሎትና መታዘዝ የሚሉትን አይተናል።ቀጥለን
የምናየው ስለራሱ ስለመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ መረጃዎችን ነው። እነዚህም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚረዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
የሚገኙ ሃገሮች፡ ከተሞች፡ መልክአ ምድሮች፣ ወንዞች፣ መንግሥታት፣ ባሕሎች፡ ገንዘቦች፡ እንስሳት፣ ትውልዶች፣ የዘር ሐረጎች፣ ጸሐፊዎች
፣አጻጻፍ፣ አነጋገር፣ ዘይቤ፣ የመጻሕፍቱን ቅደም ተከተል፣ ሥርዓተ ነጥቦች፣ ጥሬ ቃላት ወዘተ… የመሳሰሉት ናቸው። በዚህ ክፍል
የእነዚህን ጥቅም በአጭር በአጭሩ ከምሳሌ ጋር እያየን ጥናታችን እንቀጥላለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው፣ ትምህርቱም ትንቢቱም የተጻፈው በአብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በእስራኤል
ሃገር ነው። አዳም የተፈጠረበት፣ አብርሃም የተጠራበት፣ ኖኅ የጥፋት ውኃ መርከብ የሠራበት፣ እስራኤላውያን ከግብጽ ተመልሰው የወረሱት
ምድር፣ የተለያዩ የእስራኤል ነገሥታትና ነቢያት የተነሱበት፣ በሐዲስ ኪዳንም ጌታ የተወለደበት፣ ያስተማረበት፣ የሞተበት፣ የተነሳበት፣
ሐዋርያት ወንጌልን ለማስፋፋት ሥራ የጀመሩበት…. ይህ ሁሉ ከ90% በላይ የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው በእስራኤል
ሃገር ነው። ስለሆነም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሃገሮች በተለይ ስለእስራኤል ማጥናት መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ዋና ጉዳይ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከዚህ ቦታ ወደ ዚህ ቦታ ሄዱ ሲል የለቀቁትን እና የሜሄዱበትን ሃገሮች /ቦታዎች ሁኔታ ስናውቅ
ጉዳዩን ይበልጥ ትኩረት እንድንሰጠው እና መልእክቱን በደንብ እንድንረዳው ያደርጋል። ለምሳሌ አብርሃም ይኖርበት ከነበረው ከከለዳውያን
ዑር ወደ ካራን ሄደ።
« ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት
ምራቱን ሦራን ወሰደ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ ወደ ካራንም
መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ። » ዘፍ ፲፩፣፴፩።
በኋላም እግዚአብሔር ከካራን ወጥቶ ወደ ከነዓን እንዲገባ ነገረው።
« እግዚአብሔርም አብራምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም
ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። » …..«አብራምም ከካራን
በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።»…..«ወደ
ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ።» ዘፍ ፲፪፣ ፩፡፬፡፭።
የከለዳውያን ዑር በዚያ ዘመን የሰለጠኑ የሚባሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ከተማ ነበረች።
ካራን ከዑር በተሻለ የንግድ ማእከልና መተላለፍያ ስለነበረች የአብርሃም አባት ታራ ከዑር ወደ ካራን ቤተሰቡን ይዞ ሄዷል።