መጽሐፍ ቅዱስ
ሙሉ በሙሉ የዓለምና የሰው ዘሮችን ታሪክ ለመተረክ የተጻፈ / የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ በታሪክ ውስጥ በዘመናት እግዚአብሔር
ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች በቅደም ተከተል እናገኝበታለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው አከፋፈሉ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብሎ የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዳቸው ወጥ
የሆኑ የራሳቸው ታሪካዊ አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ ለአጠቃላይ ግንዛቤና ስለምን እንደሚያወሩ ለመረዳት በውስጣቸው ያለውን ታሪካዊ
ይዘት ፍሰት በጥቅል መመልከቱ አስፈላጊ ነው። በዚህም መሠረት ለዛሬ
የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ዳሰሳ እናያለን።
ብሉይ ኪዳን ከዓለም
መፈጠር እስከ ክርስቶስ ልደት ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። በዚህም ክፍል የኦሪት፣የታሪክ፣ የመዝሙራትና የነቢያት መጻሕፍት ይገኙበታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ በሆነው መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ ፲፩ ምዕራፎች መላውን ዓለም የሚወክል የነገሮችን ጅማሬ
ያሳየናል። የዓለምን አፈጣጠር፣ የኃጢአት መጀመር፣ የቋንቋ መብዛት፣ የሰው ዘር መባዛት፣ ወዘተ… ይናገራል። ከምዕራፍ ፲፪ በኋላ
ግን የአንድን ወገን ማለትም የእስራኤላውያንን ታሪክ ብቻ ይዞ ይሄዳል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው የዘመን ስፍር ፭ሺ ፭፻ መሠረት
ከዘፍጥረት ፩ - ፲፩ (ከአዳም - አብርሃም) ያለው ክፍል የ፫ሺ ፭፻ ዓመት ታሪክ ሲሆን የቀረው ከዘፍጥረት ፲፪ - ክርስቶስ ልደት
(ከአብርሃም - ክርስቶስ) ያለው የ፪ሺ ዓመት ታሪክ እንደሆነ ይነገራል። ብሉይ ኪዳን የተፈጸመው በ፭ሺ ፭፻ ዘመን ውስጥ ቢሆንም
የተጻፈው ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ፩ሺ ፬፻ ዓመት እስከ ፬፻
ዓመት- በ፩ሺ ዓመት ውስጥ ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን
ከፈጠረ በኋላ ከሰዎች ጋር በውል /ኪዳን/ ለመሥራት ለሚያዘጋጀው ለመጀመሪያው ቃል ኪዳን (ለብሉይ ኪዳን) አንድን ሕዝብ እስራኤላውያንን
በመምረጥ ለዚህም አብርሃምን በመጥራት ይጀምርና ከዚያ በኋላ መላው
ብሉይ ኪዳን እነዚህ የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት አንጻር የደረሰባቸውንና
ያደረሱትን ጉዳዮች፣ (ታሪካቸውን) ይናገራል።
የመጀመሪያው የብሉይ
ኪዳን ክፍል አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀደምት እስራኤላውያን አበው፡- አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አማካይነት እስራኤል የተባለ ሕዝብ ለራሱ
እንዴት እንደመረጠ፣ ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ በመሴ እንዴት እንዳወጣቸውና በጉዞአቸው ሕግና ሥርዓቶችን በመስጠት እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ
በማዘዝ ቃል የገባላቸውን ምድረ-ርስት ለማውረስ እንዴት እንዳዘጋጃቸው ይናገራል።