Sunday, August 26, 2012

የጥያቄ፩- መልስ


 1.  እግዚአብሔር  አዳምን  ከመፍጠሩ  በፊት  አዳም  እንደሚሳሳት ያውቃል/አያውቅም?  እንደሚሳሳት  ካወቀ ለምን  ፈጠረው?  
  ወደጥያቄው መልስ ከመግባታችን በፊት ስለእግዚአብሔር ና ስለ ሰው ባሕርያት በጥቂቱ ማወቅ  ያለብን ጉዳይ አለ። እግዚአብሔር የማይመረመር፡ ልዑልና ኃያል አምላክ ስለሆነ ስለራሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ እናውቃለን እንጂ ሙሉ በሙሉ ልንደርስበት አንችልም። የሰው ልጅ በሁለንተናው ውሱን ነው። ዓይናችን የሚያይበት፡ ጆሮአችን የሚያደምጥበት፡ እጃችን የሚዘረጋበት…. ሁለንተናችን ገደብ አለው።   ስለፈጣሪ ማወቅ አይደለም ስለፍጥረታት እንኳን ገና ያልደረስንባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስለሆነም በአስተሳሰባችን ተነስተን የእግዚአብሔርን ሃሳብና አሠራር እንዲህ ቢሆን እንዲህ ይሆናል ብለን የራሳችን ግምት ልንወስድ አንችልም። ከውስንነታችን የተነሳ።

Friday, August 17, 2012

ጥያቄ-፩


    /በድጋሜ የቀረበ/
ይህ ክፍል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ጥያቄዎችን የምንወያይበት ነው። 
    
      ፩. እግዚአብሔር  አዳምን  ከመፍጠሩ  በፊት  አዳም  እንደሚሳሳት ያውቃል/  አያውቅም? እንደሚሳሳት  ካወቀ ለምን  ፈጠረው?  
    
     ለዚህ ጥያቄ ተሳታፊዎች ከዚህ ጽሑፍ ሥር comments የሚለውን በመጫን post comment በሚለው  መላክ ትችላላችሁ። 

Thursday, August 9, 2012

ሚዛናዊነት

Mizanawinet, sebket, READ IN PDF


የሕይወታችን መመሪያ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ከምንረዳቸው ታላላቅ ቁምነገሮች አንዱ ሚዛናዊነት ነው።በውስጡ ታሪካቸው ስለሰፈረላቸው ሰዎች መልካም ተግባር ሲነግረን ደካማ የሕይወት ክፍላቸውንም ያስነብበናል።
ለምሳሌ፡-
o   የአብርሃም የእምነት አባትነትና  ------በእግዚአብሔር ፊት የነበረበትን መንፈሳዊ ድክመት
o   የዳዊትን እንደልቤነትና ----- የዝሙት ውድቀት
o   የሙሴን ጠንካራ መሪነትና---- የእምነቱን መዛል  እናነባለን።
ከውድቀታቸው እንድንማር ብርታታቸውን አርአያ እንድናደርግ መንፈስ ቅዱስ ይህን አድርጓል።
በእኛ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም። ብናወራና ቢወራልን የምንወደው የበረታንበትን ነገር ብቻ ነው። ለዚህም ይመስላል ቆመው አይደለም ሞተው እንኳ ስለድክመታቸው እንዲወራ በማይፈልጉ ሰዎች ምክንያት በየቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚነበበው የሕይወት ታሪክ የጥቂት እውነትና የብዙ ውሸት ድምር ውጤት የሚሆነው።

ክርስቲያን ግን የእውነትና የማመዛዘንን በረከት የተረዳ ነው።
በአዲስ ኪዳንም ከኃጢአት በቀር በክርስቶስ ሕይወት የምንመለከተው ይህንኑ ነው።
o   የብዙዎችን የልብ ስብራት ከአፉ በሚወጣው የሕይወት ቃል ጠግኗል።  ----- ባልተቀበሉትና ባላወቁት አፍም ተሰድቧል።
o   በምራቁ  አፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን ፈጥሯል። ----- ርኅራሄ በሚነበብበት ፊቱ ላይም ምራቅ ተተፍቶበታል።
o   ጎባጣ አቅንቷል። ----- ጀርባው እስኪላጥ ተገርፎአል
o   የሞቱትን ከመግነዝ ፈትቶ ከመቃብር አስነስቷል። ------ በአደባባይ ተሰቅሎ ስለሁላችንም ሞቷል።
ይህም (ሚዛናዊነት) በቃሉ ውስጥ ያለማዳለል ሰፍሮልናል።
   ብዙ ሕመምን ያስከተሉ ነገሮች ያላቸው መልካም ጎን ቢታወቅ ኖሮ ሀሴትን ይፈጥሩ ነበር። ሁሉም ነገር መልካምና መጥፎ ጎን ሲኖረው ቁም ነገሩ ያለው ግን ነገሮችን በመልካም ጎናቸው መጠቀሙ ላይ ነው። የአንድ ነገር ገጽታ እንደ ተመለከትንበት አቅጣጫ ይወሰናል። ስለዚህ ነገሮችን በሚዛናዊነት እንመልከታቸው።
                               « በሚጠሉኝ መሀል የሚወደኝን አገኘሁት» ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ- ገጽ ፰
                                                                                           በዲ/ን ኢዮብ ይመር
የአንድን ነገር ሙሉ ገጽታ የምናገኘው ከሁሉም አቅጣጫ (በሚዛናዊነት) ስንመለከተው ነው።
በሥነ-ሕንጻ ትምህርት አራት መሠረታዊ እይታዎች አሉ፡ - የፊትለፊት፡ የጎን፡ የላይና የውስጥ (Front, side, top and section views)። ስለዚያ ሕንጻ የተሟላ ስእል (ምስል) ለማግኘት እነዚህን አራቱንም አቅጣጫዎች  በሙሉ ማየትና መረዳት ያስፈልጋል።
ተፈጥሮአችን ራሱ ሚዛናዊ እንድንሆን ያስተምረናል። ሁላችንም በተቃራኒ  አቅጣጫ የተቀመጡ ሁለት ጆሮዎች አሉን። አእምሮአችን (ሕሊና) እና አንደበታችን (አፍ) ግን አንድ ነው። ስለአንድ ጉዳይ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ልንሰማ እንችላለን።
 ስለአንድ ነገር በአንደበታችን ከመናገራችን በፊት ነገሮችን በማስተዋል አመዛዝነን ከግራ ከቀኝ መርምረን ቢሆን አድማጭን ከሚያቆስል ንግግር እንጠበቃለን፡ ራሳችንንም ከፍርድ እንጠብቃለን።
በስፍራም፡ በአቅጣጫም  የማይወሰነው እግዚአብሔር  ከላይ ሆኖ ሁሉን ፍጹም በሆነ ሚዛናዊነት ይመለከታል። እኛ በየተመለከትንበት አቅጣጫ ፍርድን ብናዛባ፡ ሁሉም በእርሱ ፊት ግልጽ ነውና በፍትሐዊነቱ ፍርድን ያደላድላል።
ስለዚህ በምንሰማቸው ብዙ ነገሮች ሚዛናዊነት ይኑረን።  ሳናመዛዝን ለመናገርም አንቸኩል። ሁላችንም ፡ ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት በግልጽ የሚታይ ነውና።
« እግዚአብሔር በሰማይ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን። በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፡ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን።» ምሳ ፭፡፪።

Tuesday, July 31, 2012

የእግዚአብሔር ቃል

ሰማያትን ያለምሰሶ ያጸና ነው፡
«በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» መዝ ፴፫፣፮

ዓለማትን የፈጠረ ነው፡
«ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።» ዕብ ፲፩፣፫

ሰማይና ምድር ሲያልፉም ይቀጥላል፡
«ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።» ማቴ ፳፬፣፴፭።

ለዘላለም ይኖራል
«የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።» ፩ጴጥ ፩፣፳፭።

ብርቅ የሆነበት ዘመን ነበረ፡
«በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ ራእይም አይገለጥም ነበር።» ፩ሳሙ ፫፣፩።

የረሃብ ዘመን ይመጣል፡
«እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።» አሞ ፰፣፲፩።

የበረከት ምንጭ ነው፡
«በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም። » ፩ነገ ፲፯፣፲፮።

የተፈተነና ለሚታመኑት ጋሻ ነው፡
«የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው።» ምሳ ፴፣፭።

የሰው ሕልውና በቃሉም እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም
«ኢየሱስም፦ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት።» ማቴ፬፣፬

አይሻርም፡
«ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም።» ሮሜ ፱፣፮።

አይታሰርም
«ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።»
፪ ጢሞ ፪፣፱።

Tuesday, July 24, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዳሰሳ-ብሉይ ኪዳን



መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የዓለምና የሰው ዘሮችን ታሪክ ለመተረክ የተጻፈ / የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ በታሪክ ውስጥ በዘመናት እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች በቅደም ተከተል  እናገኝበታለን። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው አከፋፈሉ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብሎ የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዳቸው ወጥ የሆኑ የራሳቸው ታሪካዊ አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ ለአጠቃላይ ግንዛቤና ስለምን እንደሚያወሩ ለመረዳት በውስጣቸው ያለውን ታሪካዊ ይዘት ፍሰት በጥቅል መመልከቱ አስፈላጊ ነው።  በዚህም መሠረት ለዛሬ የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ዳሰሳ እናያለን።
ብሉይ ኪዳን ከዓለም መፈጠር እስከ ክርስቶስ ልደት ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። በዚህም ክፍል የኦሪት፣የታሪክ፣ የመዝሙራትና የነቢያት መጻሕፍት ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ በሆነው መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ ፲፩ ምዕራፎች መላውን ዓለም የሚወክል የነገሮችን ጅማሬ ያሳየናል። የዓለምን አፈጣጠር፣ የኃጢአት መጀመር፣ የቋንቋ መብዛት፣ የሰው ዘር መባዛት፣ ወዘተ… ይናገራል። ከምዕራፍ ፲፪ በኋላ ግን የአንድን ወገን ማለትም የእስራኤላውያንን ታሪክ ብቻ ይዞ ይሄዳል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው የዘመን ስፍር ፭ሺ ፭፻ መሠረት ከዘፍጥረት ፩ - ፲፩ (ከአዳም - አብርሃም) ያለው ክፍል የ፫ሺ ፭፻ ዓመት ታሪክ ሲሆን የቀረው ከዘፍጥረት ፲፪ - ክርስቶስ ልደት (ከአብርሃም - ክርስቶስ) ያለው የ፪ሺ ዓመት ታሪክ እንደሆነ ይነገራል። ብሉይ ኪዳን የተፈጸመው በ፭ሺ ፭፻ ዘመን ውስጥ ቢሆንም የተጻፈው ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ፩ሺ ፬፻ ዓመት  እስከ ፬፻ ዓመት- በ፩ሺ ዓመት ውስጥ ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ከሰዎች ጋር በውል /ኪዳን/ ለመሥራት ለሚያዘጋጀው ለመጀመሪያው ቃል ኪዳን (ለብሉይ ኪዳን) አንድን ሕዝብ እስራኤላውያንን በመምረጥ ለዚህም አብርሃምን በመጥራት ይጀምርና  ከዚያ በኋላ መላው ብሉይ ኪዳን እነዚህ የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት አንጻር የደረሰባቸውንና ያደረሱትን ጉዳዮች፣ (ታሪካቸውን) ይናገራል።
የመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን ክፍል አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀደምት እስራኤላውያን  አበው፡- አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አማካይነት እስራኤል የተባለ ሕዝብ ለራሱ እንዴት እንደመረጠ፣ ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ በመሴ እንዴት እንዳወጣቸውና በጉዞአቸው ሕግና ሥርዓቶችን በመስጠት እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ በማዘዝ ቃል የገባላቸውን ምድረ-ርስት ለማውረስ እንዴት እንዳዘጋጃቸው ይናገራል።

Friday, July 13, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ - ወንዞችና መልክአ-ምድሮች


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከእምነትና ከምግባር ቀጥሎ መረጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጥቀስ ባለፈው ሃገሮችና ከተሞች በሚል ጠቅለል አድርገን አይተን ነበር። ለዛሬ የወንዞችና መልክአ-ምድሮችን አስፈላጊነት በምሳሌ እናያለየን፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት ገነትን አጠጥቶ የሚወጣው ወንዝ ከአራት እንደሚከፈል ተጽፎአል።
« ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፣ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።» ዘፍ ፪፣፲
ለመሆኑ ገነት የሚባለው የዚያን ጊዜ የት ነበር? አሁንስ የትኛው ነው? አራቱ ወንዞች ዛሬ የትኞቹ ናቸው? መረጃ ያስፈልገናል ማለት ነው።
ቃኤል አቤልን  በሜዳ ገደለው፣ ሎጥ ወደ ተራራ ሸሽቶ አመለጠ፣ ለምን ወደ ሜዳ ወሰደው?  በሜዳ ያለ ሰው እና የሚያደርገው ነገር ለሁሉም የሚታይ ስለሆነ መሸሸግም ሆነ ማምለጥ አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የመጀመሪያው ነፍሰ-ገዳይ ቃኤል የፈጸመው በደል እንኳን ከእግዚአብሔር ከሰው የተሰወረ አልነበረም። ተራራ ግን ራስን ደብቆ ሌላውን ማየት የሚቻልበት ስትራቴጂያዊ ቦታ ነው። ሎጥ እና ሌሎችም ወደ ተራራ ሸሽተው ሲያመልጡ በመጽሐፍ ቅዱስ እናያለን።
 እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ተከፍሎ በደረቅ እንደተሻገሩ በመጽሐፍ ቅዱሰ የተገለጸ ታላቅ ተአምር ነው። እዚህ ላይ አንድ ወንድሜ የነገረኝ ቀልድ አዘል ቁም ነገር ትዝ አለኝ። ሁለቱ ጓደኛሞች አንዱ በእግዚአብሔር የሚታመን፣ ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያመሰግን፤ አንደኛው ግን ሁልጊዜ በቀልድና በፌዝ ጊዜውን የሚያባክን ነበሩ። ታዲያ የመጀመሪያው አምላኩን ሲያመሰግን እስራኤላውያንን ቀይ ባሕርን ከፍለህ ያሻገርህ አምላኬ ተመስገን፡ ተመስገን እያለ ይዘምራል። ያመስግናል።  ፈዘኛ ጓደኛው፡- አንተ ቀይ-ባሕር፡ ቀይ ባሕር ትላለህ የዚያን ጊዜ የነበረው ቀይ ባሐር በአሁኑ አንድ ኩሬ የምታክል ውሃ ነው የነበር አለው። በዚህ ጊዜ መንፈሳዊው ይህን ሲሰማ ይበልጥ እያመሰገነ ይፈነጥዝ ጀመር። እንዴ ምነው? እንደዚህ ስላልኩህ ይበልጥ ፈነጠዝክ ቢለው አምላኬ ፈርኦንንና ሠራዊቱን ኩሬ በምታህል ውኃ ማስጠሙ አስገርሞኝ ነው አለው ይባላል። የፈለገ ነገር ቢሰማ ሳይበገር ሁሉንም ነገር ለአምላኩ ክብር አዋለው።
በዚያን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹት ቀይ-ባሕር፡ ዮርዳኖስ ወንዝ ዛሬ የትኞቹ ናቸው? ምን ይመስላሉ? የሚለውን ማወቃችን መጽሐፍ ቅዱስንና የአምላክን ተአምራት በይበልጥ እንድንረዳ እርሱንም እንድናመሰግን ይረዳናል።

Saturday, June 30, 2012

መልካም እንደሆነ አየ


Melkam endehone aye, sebket, READ IN PDF
በመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ (ዘፍ ፩) እግዚአብሔር ፍጥረታትን በየቀኑ እየፈጠረ በመጨረሻ የሚናገረው ቃል «መልካም እንደሆነ አየ።» የሚል ነው። ይህም ሰባት ጊዜ ተጽፎአል። (ቁጥር ፬፡፲፩፡፲፫፡፲፱፡፳፪፡፳፭፡፴፩)።
ከርሱ በላይ ጥበበኛ የሌለ፡ ለሰዎች ጥበብን የሚሰጥ አምላክ የሠራውን ነገር ሁሉ መልካምነት የሚያረጋግጥለት ሌላ አካል ስለማይኖር ራሱ በዚህ ድንቅ ቃል እያረጋገጠ ፍጥረታትን ፈጥሯል። ሰዎች የሚሠሩትን ነገር ሰዎች ያጸድቃሉ፡ ይተቻሉ፡ ያሻሽላሉ ወይም ውድቅ ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ግን በሥራው ፍጹም ስለሆነ አንዳች እንከን ሊኖርበት ከቶ አይችልም። ሰዎች ሆነን ስንፈጠር ምንም እንኳ አዋቂነት ቢኖረንም ባለን የመረዳት አቅም ውስንነት ምክንያት ሁሉንም የርሱን ሥራዎች ለማየትም ሆነ ለመተቸት አንችልም።
አንድ የሚነገር ታሪክ አለ። ሰውየው ፈላስፋ ቢጤ ነውና በሚያያቸው ነገሮች ሁሉ አስተያየት መስጠት ይወዳል። ታዲያ አንድ ቀን መንገድ ሲሄድ ደከመውና በአንድ ሾላ ዛፍ ስር አረፍ አለ። ቀና ብሎ ሲመለከት ሾላው ዛፉ ትልቅ ነው፡ ፍሬው ግን ትንሽ ነው። አጠገቡ ደግሞ የዱባ ተክል ነበረና ሲመለከተው ዱባው ግንዱ ትንሽ ነው፡ ፍሬው ግን ትልቅ ነው መሬት ለመሬት ይጎተታል። ታዲያ ሰውየው ሁለቱን አነጻጸረና አንዲህ ሲል ተናገረ፡-
« እግዚአብሔር አነዚህን ሁለት ዕጽዋት የፈጠረ ቀን ተሳስቷል። ለትልቁ የሾላ ዛፍ ትንሽ ፍሬ፡ ለትንሹ የዱባ ተክል ትልቅ ፍሬ በመስጠት አዘዋውሮታል። ከዚያ ይልቅ ለትልቁ ትልቅ ፍሬ፡ ለትንሹ ትንሽ ፍሬ ሰጥቶ በየመጠናቸው ቢያደርጋቸው መልካም ነበረ።» አለ።
ይህን እያሰላሰለ ደክሞት ነበረና መሬት ላይ ጋደም ብሎ እንቅልፍ ያሸልበዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሆነ ነገር አፍንጫውን ይመታውና ይነቃል። ሲያይ አፍንጫው ደምቷል። ከዚያ ከደረቱ ላይ የሾላውን ፍሬ ያገኛል። ነፋስ የጣላት የሾላ ፍሬ አድምታዋለች። የርሱን አባባል አስታወሰ። እኔ ያልኩት ቢፈጸምና ያ ዱባ ከላይ ወድቆ ቢመታኝ…? …ወዲያው እንደተሳሳተ ተረዳና-- እግዚአብሔር ሆይ ያንተ ሥራ ትክክል ነው። እኔ ተሳስቻለሁ፡ ብሎ መሸነፉን አውቆ ንስሐ ገባ። አዎ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉም አንዳች እንከን የሌለበት መልካም ነው።