Thursday, August 30, 2012

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢትና የዓለም ፍጻሜ-ክፍል ፪


ባለፈው ክፍል የዓለምን ፍጻሜ አመላካች የሆኑ ከአሁን ቀደም እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው የተነሱ ሃሰተኞችን እንዲሁም በየቦታው እስከዛሬ የተካሄዱ ጦርነቶችን መረጃዎች ማየታችን ይታወሳል። ዛሬም ይህንኑ መረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል እየተፈጸመ እንደሆነ እናያለን።
ማቴ ፳፬፣፯… ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
ራብም፡
ከየትኛውም ዘመን ይልቅ በያዝነው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች በተለይ በታዳጊ ሃገሮች የሚገኙ ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ በረሃብ እየተጠቁ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። የዓለማችን የሃብት ክፍፍል እና የሕዝቦች ስብጥር ሲነጻጸር ምን ያህል ፍትሐዊ እንዳልሆንን ያሳያል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 80%  የሚሆነው የምድራችን ሃብት 20% በሆነው የዓለም ሕዝብ እጅ ይገኛል። የሚከተሉት እውነታዎች የዓለም የምግብ ፕሮግራም /World Food Program/  በተለያዩ ጊዜያት ካወጣቸው መረጃዎች የተወሰዱ ናቸው።
-      እ.ኤ.አ በ2009 ዓ/ም ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆን ሕዝብ በቂ ምግብ ማግኘት አልቻለም። ይህም ማለት የአሜሪካ፡ የአውሮፓ እና የካናዳ ሕዝብ ቢደመር እንኳ ይህን ያህል አይሆንም። በወቅቱ ከዓለማችን ከ6 ሰው አንዱ ለረሃብ የተጋለጠ ነበር ማለት ነው፡፡ ከእነዚህም 90 በመቶ በላይ የሚገኘው በታዳጊ ሃገራት ውስጥ ነው።
-      ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ምክንያት በየቀኑ 25 ሺ ሕጻናት እና ወጣቶች ለህልፈት ይዳረጋሉ።
-      ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሚኖርባቸው እስያ እና የፓሲፊክ አካባቢዎች በዓለም ከሚገኙት በረሃብ ከተጠቁት 2/3 ኛው ይገኝባቸዋል።
-      በአሁኑ ሰዓት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት /malnutrition/ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ፡ ከቲቢ እና ከወባ ከሶስቱም ድምር በላይ ሕጻናትን እየቀጠፈ ያለ የዓለማችን ችግር ነው። ከአራት ሕጻናት አንዱ የተመጣጠነ ምግብ አያገኝም። በታዳጊ ሃገራት ከ10 ሚሊየን በላይ ለሚሆነው የሕጻናት ሞት 60 በመቶ ምክንያቱ ይሄው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ከ9 ሚሊየን በላይ ለሆነው ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት ለደረሰው የሞት አደጋ ምክንያቱ ይሄው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ይህ ማለት በየ6 ሴኮንድ አንድ ሕጻን ይሞታል ማለት ነው።
-      ከዓለማችን ሕዝብ ከ7 ሰው አንዱ ራቱን ሳይበላ ይተኛል።…….

Sunday, August 26, 2012

የጥያቄ፩- መልስ


 1.  እግዚአብሔር  አዳምን  ከመፍጠሩ  በፊት  አዳም  እንደሚሳሳት ያውቃል/አያውቅም?  እንደሚሳሳት  ካወቀ ለምን  ፈጠረው?  
  ወደጥያቄው መልስ ከመግባታችን በፊት ስለእግዚአብሔር ና ስለ ሰው ባሕርያት በጥቂቱ ማወቅ  ያለብን ጉዳይ አለ። እግዚአብሔር የማይመረመር፡ ልዑልና ኃያል አምላክ ስለሆነ ስለራሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ እናውቃለን እንጂ ሙሉ በሙሉ ልንደርስበት አንችልም። የሰው ልጅ በሁለንተናው ውሱን ነው። ዓይናችን የሚያይበት፡ ጆሮአችን የሚያደምጥበት፡ እጃችን የሚዘረጋበት…. ሁለንተናችን ገደብ አለው።   ስለፈጣሪ ማወቅ አይደለም ስለፍጥረታት እንኳን ገና ያልደረስንባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስለሆነም በአስተሳሰባችን ተነስተን የእግዚአብሔርን ሃሳብና አሠራር እንዲህ ቢሆን እንዲህ ይሆናል ብለን የራሳችን ግምት ልንወስድ አንችልም። ከውስንነታችን የተነሳ።

Friday, August 17, 2012

ጥያቄ-፩


    /ሜ የቀበ/
ይህ ክፍል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ጥያቄዎችን የምንወያይበት ነው። 
    
      ፩. እግዚአብሔር  አዳምን  ከመፍጠሩ  በፊት  አዳም  እንደሚሳሳት ያውቃል/  አያውቅም? እንደሚሳሳት  ካወቀ ለምን  ፈጠረው?  
    
     ለዚህ ጥያቄ ተሳታፊዎች ከዚህ ጽሑፍ ሥር comments የሚለውን በመጫን post comment በሚለው  መላክ ትችላላችሁ። 

Thursday, August 9, 2012

ሚዛናዊነት

Mizanawinet, sebket, READ IN PDF


የሕይወታችን መመሪያ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ከምንረዳቸው ታላላቅ ቁምነገሮች አንዱ ሚዛናዊነት ነው።በውስጡ ታሪካቸው ስለሰፈረላቸው ሰዎች መልካም ተግባር ሲነግረን ደካማ የሕይወት ክፍላቸውንም ያስነብበናል።
ለምሳሌ፡-
o   የአብርሃም የእምነት አባትነትና  ------በእግዚአብሔር ፊት የነበረበትን መንፈሳዊ ድክመት
o   የዳዊትን እንደልቤነትና ----- የዝሙት ውድቀት
o   የሙሴን ጠንካራ መሪነትና---- የእምነቱን መዛል  እናነባለን።
ከውድቀታቸው እንድንማር ብርታታቸውን አርአያ እንድናደርግ መንፈስ ቅዱስ ይህን አድርጓል።
በእኛ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም። ብናወራና ቢወራልን የምንወደው የበረታንበትን ነገር ብቻ ነው። ለዚህም ይመስላል ቆመው አይደለም ሞተው እንኳ ስለድክመታቸው እንዲወራ በማይፈልጉ ሰዎች ምክንያት በየቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚነበበው የሕይወት ታሪክ የጥቂት እውነትና የብዙ ውሸት ድምር ውጤት የሚሆነው።

ክርስቲያን ግን የእውነትና የማመዛዘንን በረከት የተረዳ ነው።
በአዲስ ኪዳንም ከኃጢአት በቀር በክርስቶስ ሕይወት የምንመለከተው ይህንኑ ነው።
o   የብዙዎችን የልብ ስብራት ከአፉ በሚወጣው የሕይወት ቃል ጠግኗል።  ----- ባልተቀበሉትና ባላወቁት አፍም ተሰድቧል።
o   በምራቁ  አፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን ፈጥሯል። ----- ርኅራሄ በሚነበብበት ፊቱ ላይም ምራቅ ተተፍቶበታል።
o   ጎባጣ አቅንቷል። ----- ጀርባው እስኪላጥ ተገርፎአል
o   የሞቱትን ከመግነዝ ፈትቶ ከመቃብር አስነስቷል። ------ በአደባባይ ተሰቅሎ ስለሁላችንም ሞቷል።
ይህም (ሚዛናዊነት) በቃሉ ውስጥ ያለማዳለል ሰፍሮልናል።
   ብዙ ሕመምን ያስከተሉ ነገሮች ያላቸው መልካም ጎን ቢታወቅ ኖሮ ሀሴትን ይፈጥሩ ነበር። ሁሉም ነገር መልካምና መጥፎ ጎን ሲኖረው ቁም ነገሩ ያለው ግን ነገሮችን በመልካም ጎናቸው መጠቀሙ ላይ ነው። የአንድ ነገር ገጽታ እንደ ተመለከትንበት አቅጣጫ ይወሰናል። ስለዚህ ነገሮችን በሚዛናዊነት እንመልከታቸው።
                               « በሚጠሉኝ መሀል የሚወደኝን አገኘሁት» ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ- ገጽ
                                                                                           በዲ/ ኢዮብ ይመር
የአንድን ነገር ሙሉ ገጽታ የምናገኘው ከሁሉም አቅጣጫ (በሚዛናዊነት) ስንመለከተው ነው።
በሥነ-ሕንጻ ትምህርት አራት መሠረታዊ እይታዎች አሉ፡ - የፊትለፊት፡ የጎን፡ የላይና የውስጥ (Front, side, top and section views) ስለዚያ ሕንጻ የተሟላ ስእል (ምስል) ለማግኘት እነዚህን አራቱንም አቅጣጫዎች  በሙሉ ማየትና መረዳት ያስፈልጋል።
ተፈጥሮአችን ራሱ ሚዛናዊ እንድንሆን ያስተምረናል። ሁላችንም በተቃራኒ  አቅጣጫ የተቀመጡ ሁለት ጆሮዎች አሉን። አእምሮአችን (ሕሊና) እና አንደበታችን (አፍ) ግን አንድ ነው። ስለአንድ ጉዳይ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ልንሰማ እንችላለን።
 ስለአንድ ነገር በአንደበታችን ከመናገራችን በፊት ነገሮችን በማስተዋል አመዛዝነን ከግራ ከቀኝ መርምረን ቢሆን አድማጭን ከሚያቆስል ንግግር እንጠበቃለን፡ ራሳችንንም ከፍርድ እንጠብቃለን።
በስፍራም፡ በአቅጣጫም  የማይወሰነው እግዚአብሔር  ከላይ ሆኖ ሁሉን ፍጹም በሆነ ሚዛናዊነት ይመለከታል። እኛ በየተመለከትንበት አቅጣጫ ፍርድን ብናዛባ፡ ሁሉም በእርሱ ፊት ግልጽ ነውና በፍትሐዊነቱ ፍርድን ያደላድላል።
ስለዚህ በምንሰማቸው ብዙ ነገሮች ሚዛናዊነት ይኑረን።  ሳናመዛዝን ለመናገርም አንቸኩል። ሁላችንም ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት በግልጽ የሚታይ ነውና።
« እግዚአብሔር በሰማይ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን። በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፡ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን።» ምሳ ፭፡፪።

Tuesday, July 31, 2012

የእግዚአብሔር ቃል

ሰማያትን ያለምሰሶ ያጸና ነው፡
«በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» መዝ ፴፫፣፮

ዓለማትን የፈጠረ ነው፡
«ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።» ዕብ ፲፩፣፫

ሰማይና ምድር ሲያልፉም ይቀጥላል፡
«ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።» ማቴ ፳፬፣፴፭።

ለዘላለም ይኖራል
«የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።» ፩ጴጥ ፩፣፳፭።

ብርቅ የሆነበት ዘመን ነበረ፡
«በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ ራእይም አይገለጥም ነበር።» ፩ሳሙ ፫፣፩።

የረሃብ ዘመን ይመጣል፡
«እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።» አሞ ፰፣፲፩።

የበረከት ምንጭ ነው፡
«በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም። » ፩ነገ ፲፯፣፲፮።

የተፈተና ለሚታመኑት ጋሻ ነው፡
«የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው።» ምሳ ፴፣፭።

የሰው ሕልውና በቃሉም እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም
«ኢየሱስም፦ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት።» ማቴ፬፣፬

አይሻርም፡
«ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም።» ሮሜ ፱፣፮።

አይታሰርም
«ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።»
፪ ጢሞ ፪፣፱።

Tuesday, July 24, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዳሰሳ-ብሉይ ኪዳን



መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የዓለምና የሰው ዘሮችን ታሪክ ለመተረክ የተጻፈ / የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ በታሪክ ውስጥ በዘመናት እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች በቅደም ተከተል  እናገኝበታለን። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው አከፋፈሉ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብሎ የተከፈለ ሲሆን እያንዳንዳቸው ወጥ የሆኑ የራሳቸው ታሪካዊ አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ ለአጠቃላይ ግንዛቤና ስለምን እንደሚያወሩ ለመረዳት በውስጣቸው ያለውን ታሪካዊ ይዘት ፍሰት በጥቅል መመልከቱ አስፈላጊ ነው።  በዚህም መሠረት ለዛሬ የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ዳሰሳ እናያለን።
ብሉይ ኪዳን ከዓለም መፈጠር እስከ ክርስቶስ ልደት ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። በዚህም ክፍል የኦሪት፣የታሪክ፣ የመዝሙራትና የነቢያት መጻሕፍት ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ በሆነው መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ ፲፩ ምዕራፎች መላውን ዓለም የሚወክል የነገሮችን ጅማሬ ያሳየናል። የዓለምን አፈጣጠር፣ የኃጢአት መጀመር፣ የቋንቋ መብዛት፣ የሰው ዘር መባዛት፣ ወዘተ… ይናገራል። ከምዕራፍ ፲፪ በኋላ ግን የአንድን ወገን ማለትም የእስራኤላውያንን ታሪክ ብቻ ይዞ ይሄዳል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው የዘመን ስፍር ፭ሺ ፭፻ መሠረት ከዘፍጥረት ፩ - ፲፩ (ከአዳም - አብርሃም) ያለው ክፍል የ፫ሺ ፭፻ ዓመት ታሪክ ሲሆን የቀረው ከዘፍጥረት ፲፪ - ክርስቶስ ልደት (ከአብርሃም - ክርስቶስ) ያለው የ፪ሺ ዓመት ታሪክ እንደሆነ ይነገራል። ብሉይ ኪዳን የተፈጸመው በ፭ሺ ፭፻ ዘመን ውስጥ ቢሆንም የተጻፈው ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ፩ሺ ፬፻ ዓመት  እስከ ፬፻ ዓመት- በ፩ሺ ዓመት ውስጥ ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ከሰዎች ጋር በውል /ኪዳን/ ለመሥራት ለሚያዘጋጀው ለመጀመሪያው ቃል ኪዳን (ለብሉይ ኪዳን) አንድን ሕዝብ እስራኤላውያንን በመምረጥ ለዚህም አብርሃምን በመጥራት ይጀምርና  ከዚያ በኋላ መላው ብሉይ ኪዳን እነዚህ የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት አንጻር የደረሰባቸውንና ያደረሱትን ጉዳዮች፣ (ታሪካቸውን) ይናገራል።
የመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን ክፍል አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀደምት እስራኤላውያን  አበው፡- አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አማካይነት እስራኤል የተባለ ሕዝብ ለራሱ እንዴት እንደመረጠ፣ ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ በመሴ እንዴት እንዳወጣቸውና በጉዞአቸው ሕግና ሥርዓቶችን በመስጠት እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ በማዘዝ ቃል የገባላቸውን ምድረ-ርስት ለማውረስ እንዴት እንዳዘጋጃቸው ይናገራል።

Friday, July 13, 2012

የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ - ወንዞችና መልክአ-ምድሮች


ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከእምነትና ከምግባር ቀጥሎ መረጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጥቀስ ባለፈው ሃገሮችና ከተሞች በሚል ጠቅለል አድርገን አይተን ነበር። ለዛሬ የወንዞችና መልክአ-ምድሮችን አስፈላጊነት በምሳሌ እናያለየን፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት ገነትን አጠጥቶ የሚወጣው ወንዝ ከአራት እንደሚከፈል ተጽፎአል።
« ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፣ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።» ዘፍ ፪፣፲
ለመሆኑ ገነት የሚባለው የዚያን ጊዜ የት ነበር? አሁንስ የትኛው ነው? አራቱ ወንዞች ዛሬ የትኞቹ ናቸው? መረጃ ያስፈልገናል ማለት ነው።
ቃኤል አቤልን  በሜዳ ገደለው፣ ሎጥ ወደ ተራራ ሸሽቶ አመለጠ፣ ለምን ወደ ሜዳ ወሰደው?  በሜዳ ያለ ሰው እና የሚያደርገው ነገር ለሁሉም የሚታይ ስለሆነ መሸሸግም ሆነ ማምለጥ አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የመጀመሪያው ነፍሰ-ገዳይ ቃኤል የፈጸመው በደል እንኳን ከእግዚአብሔር ከሰው የተሰወረ አልነበረም። ተራራ ግን ራስን ደብቆ ሌላውን ማየት የሚቻልበት ስትራቴጂያዊ ቦታ ነው። ሎጥ እና ሌሎችም ወደ ተራራ ሸሽተው ሲያመልጡ በመጽሐፍ ቅዱስ እናያለን።
 እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ተከፍሎ በደረቅ እንደተሻገሩ በመጽሐፍ ቅዱሰ የተገለጸ ታላቅ ተአምር ነው። እዚህ ላይ አንድ ወንድሜ የነገረኝ ቀልድ አዘል ቁም ነገር ትዝ አለኝ። ሁለቱ ጓደኛሞች አንዱ በእግዚአብሔር የሚታመን፣ ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያመሰግን፤ አንደኛው ግን ሁልጊዜ በቀልድና በፌዝ ጊዜውን የሚያባክን ነበሩ። ታዲያ የመጀመሪያው አምላኩን ሲያመሰግን እስራኤላውያንን ቀይ ባሕርን ከፍለህ ያሻገርህ አምላኬ ተመስገን፡ ተመስገን እያለ ይዘምራል። ያመስግናል።  ፈዘኛ ጓደኛው፡- አንተ ቀይ-ባሕር፡ ቀይ ባሕር ትላለህ የዚያን ጊዜ የነበረው ቀይ ባሐር በአሁኑ አንድ ኩሬ የምታክል ውሃ ነው የነበር አለው። በዚህ ጊዜ መንፈሳዊው ይህን ሲሰማ ይበልጥ እያመሰገነ ይፈነጥዝ ጀመር። እንዴ ምነው? እንደዚህ ስላልኩህ ይበልጥ ፈነጠዝክ ቢለው አምላኬ ፈርኦንንና ሠራዊቱን ኩሬ በምታህል ውኃ ማስጠሙ አስገርሞኝ ነው አለው ይባላል። የፈለገ ነገር ቢሰማ ሳይበገር ሁሉንም ነገር ለአምላኩ ክብር አዋለው።
በዚያን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹት ቀይ-ባሕር፡ ዮርዳኖስ ወንዝ ዛሬ የትኞቹ ናቸው? ምን ይመስላሉ? የሚለውን ማወቃችን መጽሐፍ ቅዱስንና የአምላክን ተአምራት በይበልጥ እንድንረዳ እርሱንም እንድናመሰግን ይረዳናል።